Prosperity Party

የኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ ግንኙነት እመርታ ከቀጣናዊ መልህቅነት እስከ አፍሪካዊ ተምሳሌትነት የሚዘልቅ ነው- ሳምንታዊ መልዕክት

ሀገራችን ኢትዮጵያ ልዩ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ ይህ በዘመናት በወጥነት የተንጸባረቀና የተተገበረ ዓለምአቀፋዊ ግንኙነታችን ለውስጣዊ ጥንካሬ፣ ለመልካም ጉርብትና፣ ለቀጣናዊ ትብብር እና ለአህጉራዊ አንድነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ ሆኖ ዘልቋል፡፡ ይህ ሀገራዊ መርህና ፖሊሲ ከታሪካችንና ባህላችን የሚቀዳ ሲሆን በዘመናት መካከል ወጥ ሆኖ መቀጠል መቻሉ ከሀገረ መንግሥት ግንባታ መርሀችን ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ልክ እንደ ምድረ-ቀደምት የሰው ዘር መገኛነታችን ሁሉ ልንኮራበት እና ልናስተዋውቀው የሚገባን ሀገራዊ ቅርሳችንና ማንነታችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ የምትታወቅበትን የዓለምአቀፍ ግንኙነት ታሪክ እንድንዘክር ያደረገን በሰሞኑ የተፈጠረው የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲ እና የሶማሊያ መሪዎች መገናኘት ነው፡፡ ግንኙነቱ በአይነቱ ለየት ያለ፣ በዚህ ጊዜ እና በዚህ ልክ መፈጠሩ በብዙ ትንተና የሚገለጽ ተስፋ ይዞ የመጣ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ግንኙነቱ የመደመር መንግሥት ሁለተናዊ ትልሞች አንድ በአንድ እየተሳኩ የሚሄዱ መሆኑን ካሳዩ ተግባራት አንዱና ዋነኛው ሆኖ ታይቷል፡፡ 
ፓርቲያችን ብልፅግና በህዳር ወር 2012 ዓ/ም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሀገራዊና ወጥ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሆኖ ሲመሰረት አንጥሮ ከቀመራቸው ፕሮግራሞች መካከል የዓለምአቀፍና የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ፓርቲያችን አራት የዓለምአቀፍና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነጥቦችን ለይቶ የተገበረ ሲሆን እነዚህም ዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት መስጠት፣ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር እና ዓለምአቀፋዊ ትብብርን ማስፋት ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ እስካሁን አያሌ እመርታዎች የታዩ ሲሆን የኖቤል ሽልማት ከማግኘት እና የብሪክስ ሀገራት አባል መሆን፤ ከዓለምአቀፍ ኮንፈንሶች መዳረሻ እስከ የዓለምአቀፍ የትብብር ማዕከል መሆን የተዘረጉ አያሌ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ ይህ ከሀገር እስከ ዓለም በየደረጃው የሚገለጽ ስኬታማነት በፓርቲ እና በመንግሥት የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተመራ እየተተገበረ ያለ ሲሆን ዕቅዱ “ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግሥት፤ ጠንካራ መንግሥት ለጠንካራ ሀገር” የሚል ውስጣዊ መሰረትን የማጽናት ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የዚህ ውስጣዊ ጥንካሬ ፍሬ ደግሞ ከሀገርም ተሻግሮ በጎረቤት ሀገራት፣ በቀጣናው፣ በአህጉር እና በዓለም ደረጃ እየናኘ ይገኛል፡፡
ሰሞኑን  የጅቡቲና የሶማሊያ ሀገራት መሪዎች ጅግጅጋን ጨምሮ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ያደረጉት ጉብኝት ከመሪዎችና ከሀገራት ግንኙነት የተሻገረ ቤተሰባዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳየ ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በዓመቱ መጀመሪያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን  ጨምሮ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት እና የሌሎች ወዳጅ ሀገራት መሪዎች የተገኙበት መሆኑ የኢትዮጵያ ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት ከቀጣናዊ እስከ በይነ-አህጉራዊ አድማስ የሚዘልቅ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡ የሰሞኑ የኢትዮጵያ፣ የጂቡና የሶማሊያ የሶስትዮሽ መሪዎች ግንኙነትም ይህንን የዲፖሎማሲ ተቀባይነት የደረሰበትን አዲስ ምዕራፍ ገልጧል፡፡
መሪዎቹ የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውንና በሶማሌ ክልል የተሰራውን የሸበሌ ሪዘርት ምርቃት ላይ መገኘታቸው የኢትዮጵያ ሪፎርም ከቤትና ከመስሪያ ቤት ተነስቶ እንዴት ቀጣናዊና አህጉራዊ እየሆነ እንደመጣ ያሳያል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ራስዋን ብቻ ሳይሆን ጎረቤቶቿንም ጭምር አቅፋ የምትበለጽግ ሀገር መሆኗን ያስመሰከረ ግንኙነት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በመሆኑም ይህንን ከሀገር ተሻግሮ ለቀጣናውና ለዓለም የሚተርፍ የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይ በጋራ እያሳካን ወደ ፊት መገስገሳችንን እንቀጥል፡፡ የኢትዮጵያ የዓለምአቀፍ ግንኙነት እመርታ ከቀጣናዊ መልህቅነት እስከ አፍሪካዊ ተምሳሌትነት እንዲዘልቅ በማስቻል ሀገራችን በታሪኳዋና በአቅሟ ልክ የበለጸገች እንድትሆን የትውልድ አደራችንን እንወጣ፡፡ 

ብልፅግና ፓርቲ

ጥር 25፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party