የብልፅግና ፓርቲ እና የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ ልዑካን የፓርቲ ግንኙነትን ማዕከል ያደረገ ዉይይት አካሄዱ
በፓርቲዉ ፕሬዝደንት ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) መሪነት እየተተገበረ የሚገኘዉ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዉይይቱ ከዳሰሳቸዉ ጉዳዮች አንዱ የነበረ ሲሆን በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና በአፍሪካ ግዙፍ በሆነዉ ብልፅግና ፓርቲ መካከል ያለውን በማንኛዉም ሁኔታ የማይናወጥ የአጋርነት ስምምነት (All-Weather Partnership) የማጠናከር አላማ ያለዉ ነዉ።
የቻይና ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር እና ቻርጅ ዴአፌር በሆኑት በክቡር ሱን ሚንግዢ የተመራው የልዑካን ቡድን ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ እያሸጋገረ የሚገኘዉ የብልጽግና ፓርቲ ስኬቶችና ቁርጠኝነት ለአህጉረ አፍሪካም አርዓያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ከሃገራዊ ለዉጡ ማግስት አንስቶ በመላ ኢትዮጵያ በመተግበር ላይ የሚገኘዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ያስገኛቸዉን አስገራሚ ስኬቶች አበረታትዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) በበኩላቸዉ፤ የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ፓርቲው ከሚከተለዉ የመደመር ፍልስፍና ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስረድተዉ የፓርቲያችን እሳቤዎች እና መርሆዎች በቁርጠኛ አመራርና የህዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ አተገባበር የታለመላቸዉን ሃገራዊ ማንሰራራት እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሽግግር እዉን ማድረግ ወደሚያስችሉበት ምዕራፍ ተሸጋግረዋል ብለዋል፡፡ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ያለዉ ወዳጅነትም እየተጠናከረ እንደሚሄድ ያላቸዉን እምነት ገልፀዋል፡፡
በዉይይቱ ማጠቃለያ ሁለቱም ፓርቲዎች በኢኮኖሚ ልማት እና በዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማስፋት ያላቸዉን ዝግጁነት የገለፁ ሲሆን የእስካሁኑ አጋርነትም ተጨባጭ ውጤቶችን እዉን ለማድረግ ያስቻለ እንደነበር አረጋግጠዋል።