ሳምንታዊ መልዕክት- 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ አፍሪካዊ ተምሳሌትነት በፅኑ መሠረት ላይ የሚገነባበት ታሪካዊ ኩነት ነው
ምርጫ ለአንድ ሀገር ያለው ፋይዳ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ከመመሥረት እስከ ውጤታማ የሀገር ግንባታ ይዘረጋል፡፡ የውጤታማ ሀገር ግንባታ መገለጫ ደግሞ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት እስከመሆን ይዘልቃል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ተምሳሌታዊት ሀገር ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሰው ዘር መገኛ፣ በአፍሪካ ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤት፣ በዘመናዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ ያላት፣ የሉአላዊነትና የነጻነት ቀንዲል የሆነች ወዘተ የሀገር ተምሳሌትነቷ ቁልፍ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ይሁንና ይህንን የሀገር ተምሳሌትነት ክብር ላይ እንከን የሚሆኑ ጉዳዮች አልታጡም፡፡ ከነዚህም የምግብ ሉአላዊነት አለማረጋገጥ፣ ከሁለንተናዊ ድህነት አለመላቀቅ እና የዴሞክራሲ ባህል አለመገንባት የመሳሳሉ ይገኙበታል፡፡ ለዚህ ምላሽ ይሆን ዘንድ ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያ አፍሪካዊ ተምሳሌትነት ላይ እንከን የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ትክክለኛውን ጥያቄ በትክክለኛው ዘዴ በመጠየቅ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካዊ ተምሳሌት ሀገር ከፍ ለማድረግ በስትራቴጂክ ዕቅድ የታገዘ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከነዚህ ሥራዎች አንዱ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታችን ላይ የሚስተዋለው እንከን ለመቅረፍ ያለመ ሲሆን የምርጫ ሥርዓታችን ትርጉም ባለው ደረጃ በማሻሻል አካታችነትና ነጻ ምርጫን በህግና በተቋም ጭምር ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እስካሁን አያሌ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የዚህ ውጤታማነት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ ስለሆነም ስትራቴጂክ የሆነ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው በአሁኑ ግዜ መደበኛ ሥራዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት እየተሳለጡ ይገኛሉ:: በዚህ ምርጫ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥታችን መንትያ ግቦች አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ግቦቹ ምርጫው ፍትሀዊ፣ አካታች፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ እና ምርጫውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ናቸው፡፡
እነዚህ መንትያ ግቦች ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካዊ ተምሳሌት ሀገር ከፍ ለማድረግ እንደ ማስፈንጠሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ይህንን ኢትዮጵያን በታሪኳና በአቅሟ ልክ የሚገልጥ ትልቅ ዓላማ በመደገፍ ለስኬታማነቱ እንዲረባረብ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡ ለዚህም በምርጫው ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ምርጫውን ሊያሳካቸው የሚገባቸው ግቦች እና ትልቁ ዓላማ እንዲሳካ የበኩላችን አስተዋጽኦ እናበርክት፡፡
ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካዊ ተምሳሌትነት!
ብልፅግና ፓርቲ
የካቲት 2፤ 2018 ዓ/ም