ሳምንታዊ መልዕክት
39ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እና የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማድረስ ራዕይ የሚሳካ መሆኑን አመላካች ናቸው፤
በመደመር ዕሳቤ የሚመራው የብልፅግና መንግሥት በመጪው አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ይህ ራዕይ የሚሳካ መሆኑን የሚያመላክቱ ስኬቶች ከወዲሁ እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን በታላቅ ድምቀትና ድል የተካሄዱት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ እና የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ዕሳቤያችን ውጤታማነት ከማሳየት ባሻገር የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕያችን ስኬት አይቀሬ መሆኑን በጉልህ አሳይተዋል፡፡
ከመደበኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጎንለጎን የተሳለጠው የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲካሄድ መደረጉ ኢትዮጵያ የአህጉሩ ብቻ ሳይሆን የዓለምአቀፍ መናገሻነቷ እየጨመረ መምጣቱን አስመስክሯል፡፡ ይህ ስኬት በቀላሉ የመጣ ሳይሆን የመደመር መንግሥታችን በቀመራቸው የጠሩ የዓለምአቀፍ ግንኙነት ዕሳቤዎች እና በተከታታይ በሠራቸው ውጤታማ ሥራዎች የተገኘ ታሪካዊ ድል ነው፡፡
በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ከመደበኛው አጀንዳ በተጨማሪ እንደ የባህርበር ጥያቄ ያሉ የኢትዮጵያ አጀንዳዎች ጎልተው የተደመጡበት እና አያሌ የጎንዮሽ ግንኙነቶች የተካሄዱበት ነበር፡፡ በአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤው የኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተሰሚነት እያደገ መምጣቱ፣ በተከታታይ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊ ኩነቶች የማስተናገድ አቅም መፈጠሩ እና ሀገራችን የአህጉሩ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በአውሮፓ ሀገራት መካከል እየተሻሻለ ለመጣዉ መቀራረብ መሠረት መሆኗን አሳይቷል፡፡ ከመደበኛ ስብሰባዎቹ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት የሚያጎሉ የተለያዩ መስተንግዶዎች የተካሄዱ ሲሆን ይህም የገር-ሀይል ዲፕሎማሲ በመጠቀም የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡
ከዓለምአቀፍ ተቋማትና ሀገራት መሪዎች፥ ለአብነትም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ከጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒንና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት እና ሀገራት መሪዎች ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብዙ ያተረፈችበት ነው።
ሰሞኑን አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ኩነቶች በመዲናችን አዲስ አበባና በመላው ሀገራችን እየተፈጠረ ያለው ፈጣንና አስደማሚ ልማት ጎልቶ የታየበትና የተወደሰበትም ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በምሳሌነት ተጠቅሶ ትልቅ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር በሚል መሪ ቃል ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ እና ራዕዩን እስከ 2023 ዓ/ም ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ከወዲሁ በውጤታማነት የታጀቡ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡
ጉባኤዎቹ የሚያስታዉሱን ቁምነገር ቢኖር የመደመር ዕሳቤ እየተመራን ከሰራን እና እንደሀገር ከተባበርን በየደረጃው አያሌ ስኬቶች መቀዳጀት እንደምንችል ነው፡፡ ይህ የይቻላል መንፈስ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እዉን የማድረግ ግስጋሴ የሚያፋጥንና ከሌሎች የበለፀጉ ሀገራት በተስተካካይነት ለመሰለፍ የሚያስችል መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ለዚህ በገሃድ እየተሳካ ላለው የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይ ዙርያ ተሰባስበን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት ይገባል።
ብልፅግና ፓርቲ
የካቲት 9፤ 2018 ዓ/ም