ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ ነው- አቶ አደም ፋራህ
ጥር 08 2018 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን የፓርቲዉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ እና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በከምባታ ዞን የሚገኘውን የሀምበሪቾ 777 የቱሪዝም መዳረሻን ጎብኝተዋል፡፡
አቶ አደም ጉብኝቱን አስመልክተው እንደገለጹት ፓርቲው በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በልዩ ትኩረት ተግባራዊ ካደረጋቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው።
እንደሀገር በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ ለማልማትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የብልጽግና ፓርቲ እሳቤ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ትግበራ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ መነቃቃት እየፈጠረ መጥቷል ብለዋል።
ለዚህም በከምባታ ዞን የሚገኘው የሀምባሪቾ 777 የቱሪስት መዳረሻ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተራራው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዳግም በ777 ደረጃዎች እንዲለማ መደረጉን አመልክተዋል።
ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች እየለሙና እየተዋወቁ መሆኑን ገልጸው፣ ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅምም እያደገ ነው ብለዋል።
በየአካባቢው ያሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት በዘርፉ የሚገኝን ጥቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት እንደሚጠናከርም አስታውቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፓርቲው ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸሯትን ሀብቶች አልምታ መጠቀም የምትችልባቸውን ትሩፋቶች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በማልማት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝ ጥቅምን ለማሳደግ እየተሰራ ባለው ስራ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አመልክተዋል።
በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመለየትና አልቆና አርቆ በመስራት ለውጤት መብቃት እንደሚቻል ሀምባሪቾ የቱሪስት መዳረሻ ተሞክሮ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የወጣት ክንፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አባንግ ኩመዳን እንደገለፁት በፓርቲው የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ በተሰጠ ትኩረት ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስ እሳቤዎች ተግባራዊ ሆነዋል።
የሀምባሪቾ 777 የቱሪዝም መዳረሻ የፓርቲው እሳቤ ትሩፋት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የአካባቢ ፀጋን መሰረት ያደረጉ መሰል የልማት ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት በዘርፉ የሚገኝን ገቢ ከማሳደግ በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።