የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለ7ተኛው አገራዊ ምርጫ መወዳደሪያ የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር አካሄደ።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለ7ተኛው አገራዊ ምርጫ መወዳደሪያ የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር አካሄደ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር በመርሀ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ዕለቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምንከፍትበት ዋዜማ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገሪያ ፍኖተ ካርታ ለሕዝባችን የምናበረክትበት ነው፡፡
ትናንትን በመዘከር፣ ዛሬን በመሥራትና ነገን በማለም መካከል ባለው ድልድይ ላይ መሰረት የምናፀናበትና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የምናሽጋግርበትን ቃል ኪዳን የምንፈርምበት ታላቅ ቀን ነው።
ለዚህ ምርጫ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" የሚል መሪ ቃል የመረጥነው የብልፅግናችን የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር በመሆኑ ነው ብለዋል።
ተምሳሌት ሀገር ማለት በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለአፍሪካ አርአያ የምትሆን፣ በኢኮኖሚ ዕድገት የብልፅግና ማማ ላይ የምትወጣ፣ በሰላም እና በአንድነት ለቀጠናው መረጋጋት ምሰሶ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ማለታችን ነው።
የ7ኛው አገራዊ ምርጫ የብልፅግና ምልክት "የስንዴ ነዶ" ነው። ይህ ምልክት ዝም ብሎ የእህል ምስል አይደለም፤ የመደመር ፍልስፍናችን፣ የብልጽግና ስኬቶቻችን እና የአንድነታችን ወካይ መገለጫ ነው፡፡
የመደመር፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣የልዕልና፣ የሉዓላዊነት፣የበረከት እና የብልፅግና ተምሳሌት ነው፡፡
የኢኮኖሚ ነፃነታችንን፣ ከልመና አላቆ ወደ በረከት እና ወደ ራስን መቻል ለማሻገር ቃል ኪዳን የምንገባበት የብሔራዊ ክብራችን እና የኢትዮጵያ ልዕልና የሚወክል ነው።
አንድ ስንዴ ብቻውን ነዶ አይሆንም። የምርጫ ምልክትም አይሆንም፡፡ ነዶ እና የምርጫ ምልክት የሚሆነው ብዙ የስንዴ ዘንጎች በአንድነት ሲታሰሩ ነው።
ይህም አንደኛ የአብሮነት፣ የአንድነትና ጥንካሬ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስንዴ ውበት እና ጥንካሬ የሚያገኘው ሲሰበሰብ፡ ሲታሰር እና ነዶ ሲሆን ነው። በነዶ የተሳሰረ ስንዴ አይሰበርም! የተለያየ ባህል፣ እምነት እና እሴት ያለው የአስተዳደሩ ህዝብ እንደ ስንዴው ነዶ ተጣምሮና ተደምሮ የኖረ ነው። ይህ ምልክት የእኛ የአብሮነት መገለጫ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ፤ የብልፅግና ፓርቲ ውልደትና በስኬት የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ዋነኛው ዓላማ በመደመር ዕሳቤ በመመራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት የዘለቁ መዋቅራዊ ስብራቶችን መጠገንና ሁለንተናዊ ብልጽፅግና ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ህዝባችንን ድጋፍ ይዘን መጪዉን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር ዓላማ ሰንቀናል።
ብልፅግና ፓርቲ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገርነት የማሸጋገር ግብ ይዞ እየሰራ ነው፡፡
የዛሬው መድረክ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ማፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪ ምልክታችን የምናስተዋውቅበት ብቻ ሳይሆን ሀገራችን በሁሉም መስኮች ከተረጂነት ወጥታ ያላትን ዕምቅ የልማት ዐቅም ወደ ምንዳነት ቀይራ የሀገራችንን ሆነ የቀጣናችንን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች የምትፈታበት ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችሉ ጠንካራና ፅኑ መሰረቶች ላይ መቆማችን የሚያውጅ የሀገራችንን አቅጣጫ በጋራ ለመቅረፅ የምንወስደውን ታሪካዊ ሃላፊነት የሚያሳይ ክስተት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የአስተዳደሩ የመንግስትና የፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አባላት ታድመውበታል።