የብልጽግና የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር ነው- የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
የብልጽግና የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለ7ተኛው አገራዊ ምርጫ መወዳደሪያ የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር አካሄደ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመርሀ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ዕለቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምንከፍትበት ዋዜማ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገሪያ ፍኖተ ካርታ ለሕዝባችን የምናበረክትበት ነው፡፡
ትናንትን በመዘከር፣ ዛሬን በመሥራትና ነገን በማለም መካከል ባለው ድልድይ ላይ መሰረት የምናፀናበትና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የምናሽጋግርበትን ቃል ኪዳን የምንፈርምበት ታላቅ ቀን ነው።
ለዚህ ምርጫ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" የሚል መሪ ቃል የመረጥነው የብልጽግናችን የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር በመሆኑ ነው ብለዋል።
ተምሳሌት ሀገር ማለት በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለአፍሪካ አርአያ የምትሆን፣በኢኮኖሚ ዕድገት የብልፅግና ማማ ላይ የምትወጣ፣በሰላም እና በአንድነት ለቀጠናው መረጋጋት ምሰሶ የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት ማለታችን ነው።
የ7ኛው አገራዊ ምርጫ የብልጽግና ምልክት "የስንዴ ነዶ" ነው። ይህ ምልክት ዝም ብሎ የእህል ምስል አይደለም፤ የመደመር ፍልስፍናችን፣ የብልጽግና ስኬቶቻችን እና የአንድነታችን ወካይ መገለጫ ነው፡፡
የመደመር፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣የልዕልና፣ የሉዓላዊነት፣የበረከት እና የብልፅግና ተምሳሌት ነው፡፡
የኢኮኖሚ ነፃነታችንን፣ ከልመና አላቆ ወደ በረከት እና ወደ ራስን መቻል ለማሻገር ቃል ኪዳን የምንገባበት የብሔራዊ ክብራችን እና የኢትዮጵያ ልዕልና የሚወክል ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት የሀረርን ጥንታዊ ጥበብ ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ህልም ጋር የሚያስተሳስር ወርቃማ ድልድይ ሆኖ ይታየኛል፡፡
ሀረር የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የዓለም ቅርስ፣ የሰላም ተምሳሌት፣ የምስራቅ ኢትዮጵያ የንግድና የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኗ ይታወቃል በአይነ ህሊናዬ የሺህ ዘመናት ታሪክን እየቃኘሁ እና የብልጽግናን ብሩህ ተስፋ እያየሁ ነው።
ክልላችን በተለያየ እምነት፣ ቋንቋ እና ባህል ያጌጡ ህዝቦች በአንድነት ተከባብረው ተጋምደው እና ተዋደው የሚኖሩባት፣ የመቻቻል ቤተ-መዘክር ናት።
ዛሬ ሀረርን የዓለም ቅርስ ያደረጋት የቀደምት አያት ቅድመ አያቶቻችን ጠንካራ አንድነት ነው፡፡ በተናጠል ሊታሰብ የማይችለውን በህብረት መተግበር በመቻላቸው ነው፡፡
በተመሳሳይም አንድ ስንዴ ብቻውን ነዶ አይሆንም። የምርጫ ምልክትም አይሆንም፡፡ ነዶ እና የምርጫ ምልክት የሚሆነው ብዙ የስንዴ ዘንጎች በአንድነት ሲታሰሩ ነው።
ይህም አንደኛ የአብሮነት፣ የአንድነትና ጥንካሬ ማሳያ ይሆናል፡፡ ስንዴ ውበት እና ጥንካሬ የሚያገኘው ሲሰበሰብ፡ ሲታሰር እና ነዶ ሲሆን ነው። በነዶ የተሳሰረ ስንዴ አይሰበርም! የተለያየ ባህል፣ እምነት እና እሴት ያለው የክልሉ ህዝብ እንደ ስንዴው ነዶ ተጣምሮና ተደምሮ የኖረ ነው። ይህ ምልክት የእኛ የአብሮነት መገለጫ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው ፤ ፓርቲው በ"መደመር" እሳቤ በመመራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊ ስብራቶችን በመጠገን፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
ፓርቲው ህዝብን በማሳተፍ፣ በጽናትና ቁርጠኝነት ስኬቶችን ሲያረጋግጥ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የህዝብ ይሁንታ በማግኘት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውጤታማ ጉዞ ማስቀጠል የሚያስችለውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፊስቶ አዘጋጅቶ ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ማኒፌስቶው ብልፅግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ በመመራት እስካሁን ያስመዘገባቸውን ስኬቶች፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችንና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በዝርዝር የያዘ መሆንን አብራርተዋል።
ማኒፌስቷችን ትናንትን ማከምን፣ ዛሬን በአግባቡ መጠቀምንና ነገን መተንበይን ማዕከል ያደረገ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የክልሉ የመንግስትና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።