የህዝባችንን ድጋፍ ይዘን መጪዉን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሸጋገር አላማ ሰንቀናል- አቶ አደም ፋራህ
ብልፅግና ፓርቲ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቶ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገርነት የማሸጋገር ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ አስታዉቀዋል።
የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ እና የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ በተደረገበት መድረክ እንደተናገሩት: "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ መሪ መልዕክት ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀው: መጪውን ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠርና ሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የሚጠበቅበትን ሃላፋነት ለመወጣት በትኩረት እንደሚሠራም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ብሔራዊ ትርክትና ርዕይ ላይ የጋራ ስምምነት መፍጠር፣ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታትና በደሎችን በሽግግር ፍትሕ ሥርዓት የማረም ተግባርም በፓርቲው ቀጣይ የቤት ሥራዎች የተያዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በሁለቱ ውኃዎች ማለትም ዓባይና ቀይ ባሕር ላይ ያለንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ አደም፤ የመደመርና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው "የስንዴ ነዶ" የፓርቲው የምርጫ ምልክት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።