በሚራክል እውነቱ
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አሁን 73 በመቶ በላይ ደረጃ ላይ መድረሱ ይታወቃል። ግድቡ በአሁኑ ወቅት በጥሩ የግንባታ ሒደት ላይ የሚገኝና ለ24 ሰዓት ሌት ተቀን የሚታትሩ ወጣቶች እየተሳተፉበት የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ዕለት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሁሉም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች በርካታ የድጋፍ ሠልፎችን ከማካሄድ ጀምሮ አርሶና አርብቶ አደሩ፣ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁሩ፣ፖለቲከኞች፣የሀይማኖት ተቋማት፣ ባለሀብቱ፣የመንግስት ሰራተኛው በጥቅሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በዕውቀቱ ለመርዳት ቁርጠኝነቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወቅና ምናልባትም አለምን ያስደመመ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለዓለም ህዝብ ያሳየንበት አጋጣሚ የተፈጠረበት ሆኖ አልፏል፡፡
ምንም እንኳ የዘመናት ቁጭታችንን ገታ አድርገን በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ለመጀመር ከመነሻው ጀምሮ ግብፅ የዓረብ ሀገራትንና ሌሎች ሼሪኮቿንም በማስተባበር ኢትዮጵያ ለምትገነባው ግድብ ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳታገኝ ያደረገች ቢሆንም ሃገራችን እና ህዝቧ ግን ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን ግድብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውን አደባባይ ላይ ወጥተው ድምፃቸውን አስምተዋል፤አሁን ላለበት ደረጃም ማድረስ ተችሏል፡፡ በመሰረቱ ግድቡ ሃይል ከማመንጨት የዘለለ ብሄራዊ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ የተረጋገጠበት እና ብሔራዊ መግባባት የተደረሰበት የአንድነታችን ማሳያ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብፅ ግድቡ በሀገራቱ ዙሪያ ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት ሊመረምር የሚችል አጣሪ የጋራ ኮሚቴ አዋቅረው ወደ ስራ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ይሁን እንጂ እንደ ሀገር የውስጥ አንድነታችን ጠብቀን ፕሮጀክቱን ማፋጠን ሲገባን እዚህም እዛም ሁከትና አካባቢያዊ ብጥብጦች እየተነሱ የህዝብ ሰላም የሀገር ደህንነት ላይ እንቅፋት ከመሆኑም ባሻገር ግድቡ በተያዘለት ወቅት እንዳይጠናቀቅ እና አሁን ላይ ለደረስንበት ደረጃ አንዱ ምክንያት ሁኗል፡፡
ግብፅ በሶስቱ ሀገራት ድርድር ላይ ሀገረ አሜሪካ በአሸማጋይነት ጣልቃ እንድትገባ አልሲሲና መንግስታቸው ነጩን ቤተ መንግስት ደጅ ሲማፀኑ ሰንብተዋል፡፡ለዚህም ከአሜሪካ መንግስት አዎንታዊ ምላሽ አግኝታ በዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት ለበርካታ ጊዚያት ቤተ መንግስት ድረስ በመሄድ IMF እና World Bank በታዛቢነት በተገኙበት ምክክር ማድረግ ችለዋል፡፡
የኋላ ኋላ ኢትዮጵያ በቅርቡ አሜሪካ ላይ ለሚካሄደው ድርድር ዝግጅቷን ባለማጠናቀቋ ምክንያት ልትገኝ እንደማትችል አስቀድማ ብታሳውቅም ግብፅና አሜሪካ ግን የኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ አለመገኘት በአሉታ በመውሰድ ኢትዮጵያ ድርድሩ ላይ ሳትፈርም ምንም አይነት የዉሃ ሙሌት ማድረግ እንደማትችል ዶናልድ ትራምፕ መልዕክታቸውን አስተላለፉ፡፡
ይህ አይነቱ አካሄድ በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና አድሏዊ አካሄድ መሆኑን ዓለም ይገነዘበዋል፡፡ ከአደራዳሪነት ወደ ፍጹም ውሳኔ ሰጪነት ፡፡ምንም እንኳ ይህ አይነቱ ዓይን ያወጣ አድሏዊ ዉሳኔ ሰጭነት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ፍፁም ተቀባይነት የሌለውና ቁጣን ያስነሳ ጉዳይ ቢሆንም ይህንኑ አካሄድ የሚቃወሙ እንደ ሩስያ ያሉ ሀገራት ተፈጥረዋል፤በዚህ ብቻ አያበቃም በኢትዮጵያና በቡርኪና ፋሶ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን የሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል ድርድርን አስመልክቶ የአሜሪካ መንግሥት ለግብጽ እያደላ ያለ ይመስላል ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ብሄራዊ መግባባትን የፈጠረ ግድብ መሆኑ ጥርጥር የለውም። የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የፖለቲካም ሆነ የሃይማት ልዩነት ሁሉም ከልጅ እስከ አዋቂ ያሳየው ድጋፍ፣ የሃገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሳዩት ተነሳሽነት እና በግድቡ ዙሪያ የፈጠሩት አንድነት ከመቼውም በላይ እንዲቀራረቡ እና በጋራ እንዲረባረቡ ማድረጉ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር በየትኛውም ዘርፍ ለተያያዝናቸው አጀንዳዎች ትልቅ እና የገዘፈ ብሄራዊ አቅም ፈጥሮልናል፡፡
ይህን ግዙፍ እና ሰፊ ገንዘብ የሚጠይቅ ግድብ ያለምንም የውጭ ሃገራት ብድር እና እርዳታ መንግስት ሲወስን በመሰረቱ ህዝቡ ስለአባይ ያለውን ቁጭትና ከሃይል የዘለለ ሉአላዊነትን በተመለከቱ ጉዳዮች የማይደራደር እንደሆነ ስለሚገነዘብ መሆኑ አያጠያይቅም።
የግድቡ የመሰረት ድንጋዩ በኖረበት ማግስት ተጨማሪ ጥሪ ለህዝቡ ሳያስፈልግ በእልህ እና በቁጭት ተነስቷል።
በራሳችን ጥረት አባይን እንገነባለን በሚል ወኔ የተነሳው ይህ ህዝብ ለዘመናት ተጠናውቶን የነበረውን የተረጂነት እና የተመጽዋችነት መንፈስ ከጫንቃችን አሽቀንጥረን በመጣል የይቻላል መንፈስን ሰንቀን በተግባርም እንድናረጋግጥ ያስቻለን በመሆኑና የአንድነታችን ማሳያ በመሆኑ እንዲሁም ክቡር ጠ/ሚ ዶር ዐብይ አህመድ እንዳሉት ግድቡ ለሰከንድም ቢሆን ሊቆም አይችልም ፤በ2014 ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ሲሉ መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ማንም ምንም ቢል ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና የብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግስት እንደማያደርግ በቅርቡ የሚኒስትሮች ም/ቤት ስለ ህዳሴው ግድብ ባወጣው መግለጫ ላይ ሰምተናል፡፡ የሆነው ሆኖ ይህን ግድብ ፍፃሜ ላይ እንዲደርስ የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ሀላፊነት ሊሆን ይገባዋል፤ነውም: ምክንያቱም ግድቡ የእኔም፣ያንተም፣ያንቺም፣የሁላችንም ስለሆነ፡፡
ሰላም ለህዝባችን !
ሰላም ለሀገራችን !