የክልል መንግስታት ለዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል

የክልል መንግስታት ለዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል

  • Post comments:0 Comments

የክልል መንግስታት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር እና የፌደራል ተቋማት ለዐድዋ ድል መታሳቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት እያስተላለፉ ነው።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ የአድዋ ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል ነው ብሏል።

አድዋ የኢትዮጵያ ጀግኖች ክንድ ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ በታሪክ ምዕራፍ የተፃፈበት ነው ያለው የክልሉ መንግስት፥ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ነጮችን ያዋረዱበትና መቼም የማይረሳ ታሪክ ያሳዩበት ነውም ብሏል።

በጦርነቱ የኦሮሞ ጀግኖችን ሚና ያወሳው መግለጫው፥ የኦሮሞ ህዝብ ወደፊትም ለሀገሪቱ አንድነት የራሱን ድርሻ በመወጣት አሁን የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ባለበት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት መልእክት አስተላልፏል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህም 124ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ተመስገን በመልእክታቸው፥ ዓደዋ ለጥቁር አፍሪካውያን የድል ቀን እንደሆነ በመግለፅ፤ ከዓድዋ ድል ማግሥት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የሚወጡበትን ትግል ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

የዓድዋ ድል “ጥቁሮች ያሸንፋሉ የሚለውን ያረጋገጥንበትና ያስተማርንበት ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፥ ኢትዮጵያ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትኖር ተምሣሌት የሆነ ድል መሆኑንም ተናግረዋል፡።

አሁን ያለው መሪ ከዓድዋ ድል መሪዎች ለትናንሽ መሰናክሎች አለመንበርከክን፣ ቂም አለመያዝን፣ አለመከፋፈልን፣ በጫና አቋምን ያለመቀየርንና ላመኑበት ዓላማ መቆምን ሊማር እንደሚገባም ገልፀዋል።

ሀሳቦችን ከግራ ከቀኝ በመቀበልና በማመዛዘን ባመኑበት አቋም መዝለቅ ከዚያም ለሌሎችም የሚሆን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚያስፈልግም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከ ኡማም 124ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት፥ “ከ124 ዓመታት በፊት በሩቁ፣ በአሻጋሪ ተመልክተው በጨለማ የምንኖር ደካሞች አድርገው ለቆጠሩን በኀብረት፣ በእውቀት ብርሃን የምንኖር ፅኑ መሆናችንን በአድዋ አስተምረናል” ብለዋል።

“የፍቅር፣ የመተባበር፣ በጋራ የማደግ፣ የለጋስነት፣ ጎረቤትን እንደራስ የመውደድ ትምህርት ኢትዮዺያውያን ሁሌም የሚያስተምሩት የእውነት መንገድ ነው” ያሉት ኢንጂነር ታከለ፥ “የሀሰት፣ የትዕቢት፣ የመጠቃት ደንገርጋራ መንገድን ኢትዮጵያውያን እንጠላለን፣ ጠልተንም በአድዋ መንገድ እንድንፃረረው ሆነን አድገናል” ሲሉም ገልፀዋል።

“አሁንም ያ ወኔ፣ አሁንም ያ ፅናት፣ አሁንም ያ ኣንድነት ከአባቶቻችን የወረስነው በደማችንና በአጥንታችን ውስጥ እንደ ሰደድ እሳት ይክነፈነፋል” ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም “ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ለ124ኛው የአድዋ የድል በዓል መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ” ሲል መልካም ምኞቱን ገልጿል።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

Leave a Reply