አሸባሪዎቹን ትህነግ እና ሸኔ በጋራ ለመዋጋት እንደሚሠሩ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች አስታወቁ
የአማራና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በባሕር ዳር መክረዋል። ከምክክር በኋላም የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ መምከራቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የፀጥታ ጉዳይ የሚፈታውና የኢትዮጵያ አንድነት የሚቆመው በጋራ ስንሠራ ነው ብለን ተስማምተናል ነው ያሉት።
አሸባሪዎቹን ትህነግ እና ሸኔ በጋራ ለመዋጋት ክልሎቹ በጋራ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል። ፀረ ሕዝብ የኾኑ ጠላቶችን በመደምሰስ ዜጎችን ማቋቋም እንዳለብንም ተግባብተናልም ነው ያሉት። የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ ለመግታት መስማማታቸውን ተናግረዋል። ከአሁን በፊት የነበረውን ስምምነት ማደሳቸውንም ገልፀዋል።
ንጹሐንን የሚገድሉ ፅንፈኞችን መዋጋት አማራጭ የሌለው አማራጭ መኾኑንም አንስተዋል። ፅንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል እየሠሩ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በጋራ ቆሞ ፅንፈኝነትን መዋጋት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሕዝቡም ተረጋግቶ እና ሰክኖ በጋራና በአንድነት መቆም ይገባዋል ነው ያሉት።
ርእሳነ መሥተዳድሮቹ ሕዝቡና መሪዎች በአንድነት በሚሠሩበት መንገድ መስማማታቸውንም ተናግረዋል ።
ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታ ወሳኝነቱ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና ፅንፈኝነት መሆኑንም ተናግረዋል። የአማራና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ኢትዮጵያን ለማስከበር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
አሸባሪውን ሸኔ በጋራ ለመዋጋት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል ። ከአሁን በፊት በነበሩ ጉድለቶች እና ጥንካሬዎች ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም ላይ እንዳለብን ተስማምተናልም ነው ያሉት። በአጎራባች አካባቢዎች በልማት እና በፀጥታ ጉዳይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን በጋራ ለማቋቋምም ከስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው መኾኑን አንስተዋል። ችግሮችን በአሉባልታ እና በፕሮፖጋንዳ ሳይኾን በአንድነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር ተላቃ የተሻለች ሀገር አንድትኾን መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ችግሮቹን በማወሳሰብ ሊነግዱ የሚፈልጉ ፅንፈኞች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ፅንፈኞቹን በጋራ በማጥፋት በጋራ መልማት ይገባናልም ብለዋል። የተደረሱት ስምምነቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።