ሀገር የማስቀጠል ትግላችን አልተቋጨም (በፈድሉ ጀማል)

ሀገር የማስቀጠል ትግላችን አልተቋጨም (በፈድሉ ጀማል)

  • Post comments:0 Comments
ሽብርተኛው ህወሓት ህልውናውን ለማስቀጠል እንደዋነኛ መተማመኛ አድርጎ በከፈተው ጦርነት በደረሰበት ሽንፈት ከወረራቸው አካባቢዎች ተጠራርጎ ከወጣ በኋላም ላለፉት ሶስት አመታት በግልፅና በድብቅ ሲያከናውናቸው የነበሩ የጥፋት ተልዕኮዎቹን መፈፀሙን ቀጥሏል፡፡ ይህ የሽቡር ቡድን በጦርነት ተግባሩና ትንኮሳው መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮውን በተለያዩ ሴራዎችና የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳዎች አጅቦ የኢትዮጵያዊያንን ወንድማማችነትና አንድነት በመሸርሸር የእርስ በርስ መከፋፈልንና መጠራጠርን ለመፍጠር ሌት ከቀን እየተጋ ይገኛል፡፡
 
ህልውናውን ከሰላምና መረጋጋት ነጥሎ ከጦርነትና ሁከት ጋር ያጣበቀው ህወሓት ከስህተት የመማር ልምድም ይሁን ፍላት የሌለው በመሆኑ እስካሁን ከደረሰበት ሽንፈትና ውርደት እንኳን ሳይማር በጦርነት እድሜውን ለመግፋት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሆነም መገንዘብ አይከብድም፡፡
 
የሽብር ቡድኑ በራሱ ከሚያወጣቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው መግለጫዎች አንስቶ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎቹ፣ ከፍሎ ባሰማራቸውና አክቲቪስቶቹና ዓላማውን በሚጋሩት የሀገር ውስጥና የውጭ ቡድኖችና ድርጅቶች በኩል በሚያለቅቃቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ፀረ-ኢትዮጵያዊ መልዕክቶችና አስተሳሰቦች በብሄሮች፣ በሃይማኖቶችና በመንግስትና በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር እየተጋ ነው፡፡
 
ህወሃት በዚህ የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም በየአካባቢው በሚያደርጋቸው ትንኮሳዎች ላይ የተሰማራበት ዋነኛ ምክንያት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ወንድማማችነት እያደገ በሄደ ልክ የህወሓት ፀረ ኢትዮጵያዊ ከፋፋይ አስተሳሰብ ተቀባባይነት እያጣ ከሀገራችን የፖለቲካ ገበያ በመውጣት ህልውናው እንደሚያበቃለት በመረዳቱ ነው፡፡
 
ወትሮውንም ቢሆን ከሀገርና ህዝብ ዘርፎ የራሱን ካዝና ከመሙላትና በጥቅም ያደራጃቸውን ሃይሎች ሆድ ከመሙላት ያለፈ የረባ ፖለቲካዊ ግብ ያልነበረው የህወሓት ቡድን ከሀገራዊ ለውጡ እውን መሆን ጋር ህልውናው አብሮ ሊቀጥል እንደማይችል ከጅምሩ ተረድቶታል፡፡
 
የኢትዮጵያ ህዝብም ይህ ቡድን ከራሱ አልፎ ሀገርንና ህዝብን መሰረት ያደረገ ማንኛውንም የለውጥ ሀሳብንና እንቅስቃሴን ለመቀበል የሚያስችል ተፈጥሯዊ ባህሪ የሌለው መሆኑን በሚገባ ተገንዝቧል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ይህንኑ ኋላቀርና ሀገር በታኝ የህወሓት የፖለቲካ ቁማር በሚገባ ተረድተን ውስጣዊ አንድነታችንን ማፅናት ይኖርብናል፡፡
 
ከህወሓት ጋር የተጀመረው ሀገር የማስቀጠል የህልውና ዘመቻ አልተቋጨም ብቻ ሳይሆን ከፀረ ኢትዮጵያውያን ጋር የምናደርገው ትግል በቀጣይም እንደስካሁኑ ሁሉ የሁላችንንም የተባበረ ክንድ የሚጠይቅ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ በሌላ በኩል በመደበኛነት በለውጡ የተጀመሩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል እስከአሁን በተግባር ያሳየንውን ሀገር ወዳድነት በቀጣይም አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል፡፡

Leave a Reply