ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን መተው ከዘላለማዊ ጸጸት የሚገላግል ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡ፖለቲካዊ ችግራችንንም ሆነ በመካከላችን ያጋጠመንን ስንጥቅ በራሳችን አቅም እንፈታዋለን፡፡ለጊዜው በመካከላችን የበቀሉትን አረሞች እኛው በራሳችን ጥረት ነቃቅለን እናስወግዳቸዋለን፡፡ይህንን ለማድረግ በአረሞቹም ላይ ሆነ በሚወገዱበት ብልሀት ላይ የጋራ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ኢትዮጵያን በማዋረድ መላ አፍሪካውያንንና የአለም ግፉአንን ተስፋ ማስቆረጥ የለብንም፡፡
እንደጥንቱ ሁሉ የብርሀን ቀንዲልነታችንን ለአለም ህዝብ ማሳየት አለብን፡፡ ከመካከላችን እያፈነገጡ ለሉአላዊነታችን እንቅፋት የሚሆን ደባ የሚፈጽሙብንን ተላላኪ ባንዳዎች በአንድ ልብ ሆነን ልናወግዛቸው ይገባል፡፡ የውስጥ ችግራችንን በራሳችን አቅም መፍታት እደምንችል ለአለም ህዝብ ማሳየት አለብን፡፡ ተገደን የገባንበትን ጦርነት በድል አጠናቀን ድህረ ጦርነት የተናበበ የመልሶ ግንባታ ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡
ከሽብር ቡድኑ የሽብር እንቅስቃሴ አንጻራዊ ነጻነቱን ጠብቆ በከፍተኛ ፍርሀትና ስጋት ውስጥ የኖረውና በከፋ ጭቆና ውስጥ ተደፍቆና ተጨፍልቆ የቆየውን ጭቁኑን የትግራይ ህዝብና በሽብር ቡድኑ ወረራ ስር ከልክ በላይ ሲማቅቅ የባጀውን መላውን ህዝባችንን ቁስል በማከም ከሁለንተናዊ ህመሙ እንዲያገግም ማድረግና የኢትዮጵያን አንድነትና ትንሳዔ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ለአፍታም ቢሆን ተሳስተን ሊቢያ የመንና ሶርያ በቆሙበት ስፍራ ለመቆም መሞከር የለብንም፡፡
ኢትዮጵያን አሸናፊ በማድረግ የነጻነት ቀንዲልነቷን ዳግም ለአለም እናበስራለን ስንል አሸናፊነታችንን የምናረጋግጠው የሽብር ቡድኑን በመደምሰስና ዳግም የኢትዮጵያ አንድነት ጸር የማይሆንበት ደረጃ ላይ በማድረስ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚረጋገጠው የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም ድህረ ጦርነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የዜጎቿን ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት በጽኑ አለት ላይ እንመሰርታለን፡፡ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የመሆናችንን ቃልኪዳን ዳግም እናድሳለን፡፡