You are currently viewing ኢትዮጵያዊነት ከልዩ ልዩ አምዶች የተሰራ የጥበብ ቤት ነው /በሚራክል እውነቱ/

ኢትዮጵያዊነት ከልዩ ልዩ አምዶች የተሰራ የጥበብ ቤት ነው /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
ኢትዮጵያዊነት ከልዩ ልዩ አምዶች የተሰራ የጥበብ ቤት ነው
/በሚራክል እውነቱ/
 
ኢትዮጵያዊነት ሃያል ሚስጥር፣ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ሲነሳ ዓለም ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሰውነቱ ውስጥ አንዳች ነገር ሲነዝረው ይታወቀዋል፡፡ ኢትዮጵያችን በሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብላ ስትታይ ደግሞ መላ ሰውነታችን በደስታ ይንቀጠቀጣል፤ ደስታችን ገደብ ያጣል፣ ዓይናችን በደስታ እንባ ይሞላል፡፡
 
እኛ ህዝቦቿ ማንነታችንን የምናንጸባርቅበት በውድ አገራችን ኢትዮጵያ ነው፣ አንድነታችንን የምናሳይበት፣ የሉዓላዊነታችንና የነፃነታቸው መገለጫ ምልክት በሆነችው በኢትዮጵያችን ነው፡፡ የቀድሞ አባቶች የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድመው አድዋ ላይ የውጭ ወረራን ድል አድርገው ከራሳቸው አልፈው የጥቁር ህዝቦች ክብርና መንፈስ ከፍ እንዲል ያደረጉት ኢትዮጵያዊነት መሰረቱ የጸና በመሆኑ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያዊነት ከልዩ ልዩ አምዶች የተሰራ የጥበብ ቤት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በትዕግስት የታሸ ጀግንነት ነው፡፡ ጨዋነታቸው ወይም ያልነኳቸውን አለመንካታቸው፣ አገር ወዳድነታቸው፣ ለነፃነት ያላቸው ፍቅርና ታሪክ በደማቁ የተፃፈላቸው የጀግንነት ገድላቸው፣ የሞት ፍርሃትን መፀየፉቸውና ታሪክ ሰሪነታቸው የዚህ ምስክሮች ናቸው-ለኢትዮጵያዊያን።
 
ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነት የራቀ ማህበራዊ ፍቅር ወይም ከራስ ወዳድነት የተለየ የወገን ተቆርቋሪነት ነው፡፡ ግብዝነት የሌለበት ወንድማማችነት፣ የማስተዋል ደግነትና እንግዳ ተቀባይነት፣ መቻቻላቸውና አስታራቂነታቸው፣ በሰው አክባሪነታቸውና በጓደኛ መካሪነት ጭምር የሚገለጡት ስብዕናቸው ለማህበራዊ ፍቅራቸው ምስክሮች ናቸው፡፡
 
ኢትዮጵያዊነት ጨዋነትና ግብረ ገብነትን ያመላክታል፤ ቀናነትንና የልብ ንጽህናን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ይታያል፣ ኢትዮጵያዊነት ትህትና ያልተለየው፣ የክብር መንፈስ ወይም የክብር ፀጋ የማይለየው እውነታ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያዊነት የሕዝቧን አንድነት፣ የመንግሥቷን ቀጣይነት፣ የግዛቷን ሉዓላዊነት፣ የዜጎቿን እኩልነት የሚያቀነቅን የአብሮነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በርዕዮታዊ፣ ባሕላዊና ታሪካዊ አንድነት ላይ የቆመ ማንነት ነው፡፡
 
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ህልውና ያላት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ይህን አገራዊ ህልውና የሚያንፀባርቁ የበርካታ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ረቂቅም ግዙፍም፣ ህሊናዊም ነባራዊም፣ ታሪካዊም ባህላዊም፣ ፖለቲካዊም ማህበራዊም መልኮችና በውስጡ የያዘ ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!

ምላሽ ይስጡ