የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ር/መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል
“አሸባሪውን የህወሓት ኃይል እየመከትን የልማት ስራዎቻችንም እናስቀጥላለን” ያሉት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤
ሀገራዊ፣ ወቅታዊና ክልላዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግሥትና ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ ጁንታው የህወሓት ቡድን ላለፋት 27 ዓመታት ሙሉ ሀገሪቷን የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥሮችን በመፊጠርና በመበዝበዝ ለራሱ በሚመቸው መልኩ የግልና የቡድን መብቶችን ሲጥስ መቆየቱን አንስተው ይህ አሸባሪ የህዝብ ደም መጣጭ ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብን ዳግም ለመበዝበዝ ካልተሳካለትም ሀገሪቷን ለመበታተ አልሞ ከሌሎች አመድ አፋሽ ኃይሎችን በመፈለግ ግልፅ ጦርነት መክፈቱን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው ላይ አክለውም ይህ እብሪተኛ የጁንታ ኃይል የሚያደርገውን መፍጨርጨር በአስተማማኝ መልኩ ለመመከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው የሲዳማ ክልል ህዝብም ይህንን ጁንታ ኃይል ለመመከት የህይወት መስዋትነት እየከፈለ ለሚገኘው ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ደጀን እና ድጋፍ መሆኑን ለማሳየት የክልሉ ህዝብ እና መንግስት የተለያዩ አስተዋጽዖችን እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ ድጋፋም ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በመግለጫቸው ማጠቃለያ ላይም እንደተናገሩት የክልሉ ህዝብ እና መንግስት ለመከላከያ ሰራዊታችን ደጀን መሆኑን በድጋሚ ለመግለጽ በሶስት የክልሉ ከተሞች ከነገ 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ ደማቅ የድጋፍ ሰልፎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።