You are currently viewing የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ

  • Post comments:0 Comments
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ
የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ ኢትዮጲያን ከተደቀነባት የውስጥና የውጭ ፈተና ለመታደግ እዘምታለሁ፤የትም፤መችም፤ በምንም የሚለዉን ሀገራዊ መሪ ቃል በተጨባጭ በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
አሸባሪዎቹ ሕወሐት/ጁንታና ኦነግ-ሸኔ ግንባር ፈጥረው የወጠኑትን ሀገርን የማፍረስና እልቂትን የመፍጠር አጀንዳ በማምከን ሀጋራዊ ሉኣላዊነትና ነፃነት ያላንዳች መንገራገጭ ለማስቀጠል ዘብ ቆመዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የሉኣላዊነታችን ጋሻና መከታ ለሆነው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ደጀን ለመሆን ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከወጣት እስከ አዛውንት፤ አንድም ሳይቀር በኢትዮጲያዊነት የማሸነፍ ወኔ የተቃኘው የክልላችን ሕዝብ የተባበረ ክንድ በሚታይም ሆነ በስውር ኢትዮጲያን ለማፍረስ ያሰፈሰፉ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን አስደንግጧል፡፡
ሕዝቡ በገንዘብና በቁሳቁስ ጀግናውን የመከላከያ ሠራዊታችንን ከመደገፍ አልፎ በተለይ ወጣቱ በአካል ሠራዊቱን በመቀላቀል እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል ያሳየው ጀግንነትና ቁረርጠኝነት ታሪክ የማይረሳው ነው፡፡
ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ጠንካራ ደጀን ለመሆን የተጀመረው እንቅስቃሴ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ሀገርን ለመታደግ በተወጠነው መረሀ ግብር ጀግናው የክልላችን ህዝብ በሁሉም የትግል አውድ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ከትንሹ ቁሳዊ አስተዋፅኦ እስከ ሕይወት መስዋትነት ለመክፈል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለው ብቻ ሳይሆን የለለውም ጭምር በሚችለው ሁሉ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ተሰልፏል፡፡
በዚህ ፈታኝ ምዕራፍ ኢትዮጲያን ለማዳን ሁሉ-አቀፍ ርብርብ በምናደርግበት በዚህ ወቅት ሁኔታዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማይገባውን ሀብት ለማካበት የሚውተረተሩ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳሉ ተደርሶበታል፡፡ እነኚህ ራስ ወዳድና ለህዝብና ሀገር ደንታ የሌላቸው ግለሰቦችን በኢትዮጲያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተው ከአሸባሪው የ ሕወሐት ጁንታ ለይተን አናያቸውም፡፡
ስለሆነም፤ ያለ ዕውቀት ሀብት ለማካበት ብቻ በዚህ የሀገርና ህዝብ ክህደት ተግባር ውስጥ የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች እጃችሁን በፍጥነት እንድትሰበስቡ መንግስት ያሳስባል፡፡ በአመለካከትና በድርጊት የባንዳነትና ተላላኪነት ተግባር ለመወጣት የንግዱን ስርዓት ለማዛባት በዘመታችሁ ቡድኖች ላይ መንግስት አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ይገልፃል፡፡
ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲጋለጥ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሂዳት ውስጥ የተሰጠውን ሃላፊነት በመዘንጋት የህዝቡን መብትና ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ በተገኘ የመንግስት የስራ ሃላፊም ሆነ ባለሙያ ላይ መንግስት የማያወላዳ እርምጃ እንደሚወስድ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
ኢትዮጲያን ለማዳን እዘምታለሁ፤የትም፤መችም፤ በምንም!
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ፤ 2013
ፊንፊኔ

ምላሽ ይስጡ