ኢትዮጵያ ያካሄደችው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመልካም ሁኔታ ተጠናቋል – የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን
በኢትዮጵያ የተደረገው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ እና ተዓማኒነትን በተላበሰ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁን የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ገለጸ።
ቡድኑ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የምርጫውን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ተዘዋውሮ መታዘቡን ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ምርጫው ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላማዊ ሁኔታ መከናወኑን ነው የኅብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ በሰጠው የመጀመሪያ መግለጫ ያሳወቀው።
የታዛቢ ቡድኑ መሪ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንዳሉት፤ ምርጫው በሰላም፣ ሥርዓቱን በጠበቀ እና ተዓማኒነት ባለው ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ታዛቢ ቡድኑ ምርጫውን የታዘበው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2007 በወጣው የኅብረቱ የዴሞክራሲ፣ ምርጫና አስተዳደር ቻርተር መሰረት መሆኑ ተገልጿል።
በአፍሪካ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስተዳደርን በተመለከተ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ2002 የወጣውን የመርህ ድንጋጌም መሰረት ማድረጉን ታዛቢ ቡድኑ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።