በሚራክል እውነቱ
በሀገራችን የሚገኙ ምሁራን እንዲህ ሲሉ አዳምጠን ይሆናል፡፡ ሰዎች፣ግለሰቦች ወይም ትውልድ ያልፋል ሀገር ግን ትቀጥላለች ይላሉ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ሀሳብ ብዙዎቻችንን ያስማማል ተብሎ ይታሰባል፡፡ምንም እንኳ በትውልድ ቅብብሎሽ መካከል ከፍና ዝቅ ቢኖርም፡፡
እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓይን የሚታይ፣በእጅ የሚዳሰስ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ይህ ደግሞ በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃም ጭምር ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ሰፊውንና ፈጣኑን የለውጥ መንገዷን መነሻ አድርጋ መዳረሻዋን ከብልፅግና ማማው ከፍታ ላይ ለማስቀመጥ ከጊዜ ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ገብታለች፡፡
ወደዚህ አይነቱ የለውጥ ሀዲድ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ግን በአንዳንድ ወገኖች በኩል የሚታዩ አላስፈላጊ ተግባራት የህዝብን ሰላም የሀገርን ደህንነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ አያሌ ምልክቶች ተስተውለው አልፈዋል፡፡
የራስን የፖለቲካ አጀንዳ ከአገር በማስበለጥና ሕዝቡን በብሔር በማቧደን ለማበጣበጥ መሞከር፣ በማንነት ስም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እያደበዘዙ ማጥፋት፣ ሌላው ወገን በደል ያልደረሰበት ይመስል የራስን እያጦዙና እያጎኑ የአገር አንድነትን ማፍረክረክ፣ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን የብተና ፖለቲካ ሲያራምዱ በዚህም ህዝብን ወደ ግጭት ሲመሩ ታዝበናል፡፡
በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብን አደራጅቶ በፅናት ከመታገል ይልቅ በባዕዳን ጉርሻ በመደለል አገር ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ በአስተዳደራዊና በሌሎች ምክንያቶች የሚደርሱ በደሎችን ከለላ በማድረግ አገርና መንግሥትን የማይለይ ቀውስ ለመፍጠር መሯሯጥ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ለዘመናት በተካሄደ ትግል በተገነባ ዴሞክራሲ ውስጥ በነፃነት እየኖሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ከማድረግ ይልቅ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የእልቂት ነጋሪት ሲጎሰምባት ሰምተናል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ባህርይ አይደለም፡፡
አሁን ያ ሁሉ አለፈና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረውን ፍቅር፣ መከባበርና መደጋገፍ እንደገና ወደነበረበት በማስቀጠል፣ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ እንደተናገሩት አንዱ ጎታች ሌላው ተጎታች ሳይሆን ወይም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሳይሆን ሁሉም እኩል ለሀገሩ ብልፅግና አሻራውን የሚያሳርፍበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል የሆነችና የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖር በጋራ ጉዳዮች ላይ በነፃነት በመነጋገር ዴሞክራሲን በተግባር ማረጋገጥ ተችሏል ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከሰራቸው ስራዎችና ካመጣቸው ለውጦች ይልቅ ገና ወገብ የሚያጎብጡ ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውጤት ለማምጣት ርብርብ እያደረገ የሚገኝ ፓርቲ ነው፡፡ ምክንያቱም ብልፅግና በዕውቀትና በዕውነት ላይ የቆመ ፓርቲ ነውና፡፡
በግለሰቦች መሄድና መምጣት አቋሙ የማይለዋወጥ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሌት ተቀን የሚጥረው ብልፅግና ሀቀኛ፣ትክክለኛና እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲተገበር አበክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ህዝቡ ብልፅግና ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጎን በመሆን የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሕገ ወጦች አደብ እንዲገዙ ከምንጊዜውም በላይ አጋርነቱን እያሳዬ ይገኛል፡፡ ሁሉም ነገር በሕጉ መሠረት ሲከናወንና የሕዝቡም እርካታ በግልጽ ሲታይ፣ አመፅና ብጥብጥ ቦታ አይኖራቸውም፡፡
የዚህች ታላቅ አገር ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ለህግ የበላይነት በሁሉም ቦታ መከበር፣ዜጎች የሰላም አየር መተንፈስ እንዲችሉ፣ለሚያጋጥሙ ሀገራዊ ችግሮች በጠረንጴዛ ዙሪያ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅና ለመሳሰሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ለጋራ ብልፅግና በጋራ መነሳት ከቻልን አይቀሬውን የሀገራችን ኢትዮጵያ ብልፅግና በብልፅግና ፓርቲ ዕውን መሆኑ አይቀርም፡፡
ትናንትም፣ዛሬም ነገም እንደምንለው ሰላም ለሀገራችን፤ ሰላም ለህዝባችን !!