You are currently viewing

  • Post comments:0 Comments

በሚራክል እውነቱ

ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያሰኟት በጉያዎቿ አቅፋና ደግፋ የያዘቻቸው ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ከሰሜን እስከ ደቡብ ድረስ ባሉና በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ ናቸው፡፡በርግጥም ይህ ህዝብ ለዘመናት ክፉውንም ሆነ ደጉን ጊዜ አብሮ አሳልፏል፡፡ችግርህ ችግሬ ደስታህም ደስታዬ ነው፣ካንተ በፊት እኔን ያድርገኝ የሚል ደግ ህዝብ፡፡

በመንገድ ላይ እንኳ ጎን ለጎን ስንጓዝ እንቅፋት ቢመታን እኔን በሚልና ካንተ በፊት ያስቀድምኝ በሚል ልባዊ ወንድምነቱን የሚገልፅ ደግና አስተዋይ ህዝብ ነው፡፡ሰው ታሞ በበሽታ ሲሰቃይ ሩቅ ተጉዞ ፌጦውን፣ተልባውን፣ሀረግሬሳ፣ግራዋውን ብቻ ለወገኔ ፈውስ ይሆነዋል ብሎ የሚያስበውን ሁሉ አምጥቶ አድርቆም ሆነ አፍልቶ የሚያቀርብ የዋህ ህዝብ፡፡

ታዲያ ለዘመናት በፍቅርና በአብሮነት አንተ ትብስ አንቺ እየተባባሉ ዕምነትና ብሔር እንቅፋት ሳይሆናቸው የኖሩት ሁሉም ሰዋዊ ፍላጎቶቻቸው ተሟልቶላቸው አይደለም፡፡በበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ከዛሬ ነገ የተሻለ ይሆናል፣የሚያጋጥሟቸውን ጊዚያዊ እንቅፋቶች በሙሉ የነገዋን በብሩህ ተስፋ የተሞላች ኢትዮጵያን እንዳይጋርዳቸው ችለውና ታግሰው ሰለኖሩ እንጂ፡፡

ለአያሌ ዘመናት የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ታፍነውና ተጨፍልቀው ሲኖሩ ዝም ያሉት በብርሀን የተሞላችና በህዝቦቿ ሁለንተናዊ ትብብር ያደገችና የበለፀገች አዲስ ኢትዮጵያን የማየት ጉጉታቸው ከፊት ለፊታቸው ስለሚታያቸው እንጂ፡፡

አብሮነታችን የአንድነታችን ማሳያ፣ህብረ ብሔራዊነታችን የማንነታችን ፋኖስ ሆኖ ረዢም ዕድሜን ያስቆጠረች ሀገር አሁን አሁን ሰላሟን የሚነጥቃት አያሌ ችግሮች ከፊት ለፊቷ ተጋርጧል፡፡አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን የብሔር ስያሜ እየተሰጣቸው በህዝቦች መካከል ክፍተት እንዲፈጠር እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩ ሀይሎች አይጠፉም፡፡

እርግጥ ነው በችግርና በስቃይ ጠመዝማዛ መንገድ ሳያልፍ ያለፈለት ህዝብም ሆነ ሀገር በዓለም ላይ ከቶውንም አይገኝም፡፡ግን ደግሞ በእያንዳንዷ ኮሽታ ከመደናገጥ ይልቅ አቅልን ሰብሰብ አድርጎ ከችግሮቹ ጀርባ ከሚታየን ወጋገን ለመድረስ ፅናት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡

ለዘመናት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የመኖራችን ሚስጥር የመቻቻልና የመተሳሰብ ፣የመከባበርና የአብሮነታችን ማህበራዊ እሴቶች በአንድነት ገመድ ስላጋመዱን እነሱኑ ጠብቀን በማስጠበቃችን ምክንያት ነው፡፡ይህ ማለት ግን እነዚህ ማህበራዊ እሴቶቻችን አሁን ላይ አጠናቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ደጋግ ኢትዮጵያዊያን አሉና፡፡በችግር ጊዜ የችግሩ ወላፈን እንዳያገኛቸው በቤታቸው ታዛ አስጠልለው እያበሉና እያጠጡ የሚያኖሩ የደግ ህዝቦች ባለቤት ናት ሀገራችን ኢትዮጵያ፡፡

እርግጥ ነው እንደነዚህ አይነት ኢትዮጵያዊያንን ስንመለከት ከቶውንም በሀገራችን ላይ ተስፋ ልንቆርጥ አንችልም፡፡እንዲያውም እያንዳንዳችንን የበጎነትን ሚስጥር ያስተምረናል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያዊነት በትንንሽ እንቅፋቶች ተጠልፎ የሚወድቅ ማንነት ሳይሆን እንደ አለት የጠነከረ፣ እንደ ወርቅ በእሳት የተፈተነ ፅኑ ማንነት እንጂ፡፡

ስለዚህ በዚህ ወቅት የሚያጋጥሙንን ጊዚያዊ ችግሮች የህግ የበላይነት ማስከበሩ እንዳለ ሆኖ እኛነታችን ሊለያዩ ከሚፈልጉ ሀይሎች ራሳችንን በማራቅ የቀደመውን አብሮነታችንን በፍቅር መልሰን በከፍታው ማማ ላይ ከፍ በማድረግ ዳግም አንድነታችንን ልናሳይ ይገባል፡፡

በህብር ወደ ብልጽግና !

ምላሽ ይስጡ