You are currently viewing ጁንታው አስከሬን ላይ በታንክ እስከመሄድ ግፍ ፈጽሞብናል .. የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት

ጁንታው አስከሬን ላይ በታንክ እስከመሄድ ግፍ ፈጽሞብናል .. የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት

  • Post comments:0 Comments

የህወሃት ቡድን በውድቅት ሌሊት ባደረሰብን ጥቃት አስከሬን ላይ በታንክ እስከመሄድ ግፍ ፈጽሞብናል ሲሉ ከጁንታው ቁጥጥር ስር ወጥተው በሰቆጣ በኩል የገቡ የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት አስታወቁ።ጁንታው ያሰማራቸው የቡድን አባላት “ሌሊት በተኛንበት ባትሪ እያበሩና እየለዩ የሰራዊቱን አባላት ገድለዋል” በማለት የእዙ አባላት ለኢዜአ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሰሜን እዝ የአራተኛ ክፍለ ጦር አባል ምክትል አስር አለቃ ገብረሚካኤል ጌታነህ እንደገለጹት የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ተወጣጥቶ የተዋቀረ ነው፡፡በትግራይ ክልል የሚገኘው የሰሜን እዝ ሰራዊት አባላትም በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ተመድበው በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ በልማትና በበጎ አድራጎት ስራ እየተሳተፉ እደነበር ጠቅሰዋል፡፡

“ህብረተሰቡን እንደቤተሰብ አድርገን እየኖርን ባለበት ሁኔታ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በክፍለ ጦሩ ውስጥ ባሉ በትግራይ ተወላጅ አባሎች ተኩስ ተከፍቶ እጅ እንድንሰጥ ተጠይቀናል” ብለዋል፡፡በእለቱ አብረው ለጥፋት በተሰለፉ በጁንታው የልዩ ሃይል አባላት አማካኝነት መታፈናቸውን የተናገሩት አስር አለቃ ገብረሚካኤል ከታፈኑ በኋላም የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች እየተለዩ ግድያ ይፈፀምባቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ከግድያው በኋላም በሰራዊቱ ሬሳ ላይ በታንክ በመሄድ አሰቃቂ ተግባር እንደፈጸሙም በማስረዳት፤ በጁንታው ዘይዘው በነበሩበት አጉላ በተባለው አካባቢም ከፍተኛ ድብደባ ይፈፀምባቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡”እኛ አሁን እንደገና ታጥቀን ያልተለቀቁ የሰራዊት አባሎቻችን ለማስለቀቅ እንፈልጋለን” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ሀምሳ አለቃ ክፍሌ ጊምባ በበኩላቸው ሰራዊቱ በተኛበት እጅ እንዲሰጥ በመጠየቅ መሳሪያቸውንና ትጥቃቸውን እንደወረሷቸው ጠቁመው፤ አግበ አካባቢ በነበሩበት ወቅትም በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ ይሰጧቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በቆይታቸውም ድብደባና ግርፋት ይደርስባቸው እንደነበር ያወሱት ሀምሳ አለቃ ክፍሌ፤ በምሽት ተከዜ ወንዝ ወስደው እንደጣሏቸው ተናግረዋል፡፡በተከዜ በኩል ወደ ዋግ ኽምራ ከገቡ ወዲህ ምንም አይነት ችግር እንዳልደረሰባቸውና ህብረሰተሰቡ እንክብካቤ እያደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሰሜን እዝ ተመድበው በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ለአስር አመታት መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ሀምሳ አለቃ እምቢያለ ስሜ ናቸው።”እንደዚህ ያለ ግፍ በወገናችን ይደርስብናል ብየ አስቤ አላውቅም” ሲሉ በጁንታው የተፈጸመባቸውን መሪር ጥቃት ገለጸውታል።

“እኛን ሲመሩ የነበሩ የክፍለ ጦር አመራሮቻችን ለጽንፈኛው የህዋሃት ታጣቂ አሳልፈው ሰጥተውናል” ያሉት ሀምሳ አለቃ እምቢአለ አመራሩ ቆራጥ የሆኑባቸው ክፍለ ጦሮች ራሳቸውን በመከላከልና የማጥቃት እርምጃ በመውሰድ የጁንታው አባል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማድረስ ጀግንነት መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡በጁንታው ቁጥጥር ስር የነበሩ 1139 በላይ የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከትላንት በስትያ ጀምሮ በሰቆጣ በኩል መግባታቸው ታውቋል።

ምላሽ ይስጡ