You are currently viewing ጥንቸል ናችሁ ሲባሉ ነብር ነን ያሉ ህዝቦች

ጥንቸል ናችሁ ሲባሉ ነብር ነን ያሉ ህዝቦች

  • Post comments:0 Comments

ኤስሮም ፍቅሩ

የገቡበት የመከራ ጥልቀት እንዲህ በቀላሉ አይገለፅም፡፡ ጀርባቸው ላይ ያላረፉ የመጥፎ ታሪከ አሻራዎች አልነበሩም፡፡ ድህነት፣ ረሀብ፣ ስደት፣ ጦርነት እና ግዞት ሁሉም በየፈርጁ ተፈራርቀው ተስፋ ቢስነት ውርሳቸው እንዲሆን አስቀያሚ ገፅታን አልብሰዋቸዋል፡፡
የሚመኩበት የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው፤ ያላቸውን በአግባቡ መጠቀም እንኳን እንዳይችሉ በግዞት ስር የወደቁ፤ የፖለቲካ ሽኩቻ ጥሪት አልባ አርጎ ለዘመናት የቀረፃቸው ሆነዋል፡፡ ታሪካቸው ላይ በበጎ እንኳን የሚከተብ የሚለቀም ጠፍቷል፡፡
ድልን እንዳይፅፉ ተንበርክከዋል፤ ጥጋብን እንዳይፅፉ ተርበዋል፤ ትውልድን እንዳያስቡ ያለው መክኗል፤ ሴቶች ተመርዘው ወንዶች በባርነት ስር ወድቀዋል፡፡
ታሪኩ ለማመን የሚከብድ ቢሆንም ከዛሬ 65 አመት በፊት የነበረ የዛሬዎቹ የደቡብ እና የሰሜን ኮሪያ ከፍቺ በፊት የተቋደሱት የጋራ ታሪክ ነው ! ባለቤቶች ደቡብ ኮሪያውያን!
በኮሪያውያን ታሪክ እኤአ ከ1910 እስከ 1945 ባሉት 35 አመታት በግዞት የነበሩበት የስብራት መጠን ሊጠገን የሚችል አይመስልም ነበር፡፡ የጃፓን ወረራ ተብሎ በተጠራው የያኔው ግፍ የደረሰባቸው የሰብአዊነት፤ የሞራል፤ የጦርነት ኪሳራ ቀላል አልነበረም፡፡ ከምንም በላይ ወረራው ትኩረቱ ኮሪያውያንን በሁለመና ማድቀቅ እና ማንበርከክ ስለነበር በጃፓን በኩል እጅግ የተጠና ስነልቦናዊ የማዳከም ስራ ይሰራባቸው ነበር።
በተለይም የካርታቸው ቅርፅ “ተዳክማ እግሯን ወደ ላይ ያደረገች ጥንቸል ይመስላል” በማለት ደካማ እና ሰነፍ ህዝቦቸ ናቸው የሚል ትርክት እንዲሰርፅ ለ3 አስርት አመታት ሰርተዋል።
ከጊዜ በኋላም ነገሮች ተቀያይረው ጃፓን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ተሸንፋ፤ ኮሪያም ከአንድ ወደ ሁለት ደቡብ እና ሰሜን ሆና ተሰንጥቃ በደካማ ጥንቸል ሲመሰል የኖረው ካርታ ቅርፁ ቢለወጥም በተለይም ደቡብ ኮሪያውያን ከደካማ እና ሰነፍ ጥንቸልነት ስነልቦና ለመላቀቅ ከብዷቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ያንን የግዞት ስነልቦና ለመቀየር እና የአሸናፊነት ብሎም የድል አድራጊነትን ስነልቦናን ለመቀናጀት በጃፓን ጥንቸል ተደርጎ የተመሰለውን “የለም ስህተት ነው እኛ በደካማ ጥንቸል ሳይሆን በአሰፍሳፊ ነብር መመሰል የሚገባን ህዝቦች ነን” በሚል እሳቤ ተክተው ጉዞ ጀመሩ፡፡
ጥንቸልን በነብር የተካው የነፃነት ትርክትም ፍሬ እንዲያሳይ እና ለሀገር ግንባታ ጡብ መሆን እንዲችል ደቡብ ኮሪያውያን ራሳቸውን በአሰፍሳፊ ነብርነት ስነልቦና የቀረፁበት መንገድ እውነተኛ ፍሬ አፈራና በነብር እንጂ በጥንቸል ሊመሰሉ የማይገባቸው መሆኑን ማስመስከር ቻለ፡፡
የነብርን ድፍረት፤የአይኖቹን የትኩረት ብቃት፤የጥፍሮቹን ጉልበት፤የደፈጣ ጥበቡን ረቂቅነት እያስተዋሉ በአሸናፊነት ስነ-ልቦና ወደ ብልፅግና መገስገስ ጀመሩ፡፡
በአጭር ጊዜም ድካማቸው ፍሬ እያፈራ፤የነብርነት ትርክት ጥንቸሏን እየዋጣት፤ግዞት ማንነታቸውን የትላንት ታሪክ ትኩረታቸውን ያልሰረቃቸው በረሃን ወደ ገነት መቀየር የሚችል ትንታግ ሆነው ታዩ፡፡
ትላንት ይሄ ነው የምትለው መኩራሪያ ያልነበራት ደቡብ ኮሪያ ዛሬ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ የኢኮኖሚ ባለቤት፤የቅንጦት ኑሮ ምሳሌ፤የፈጠራ ሰገነት፤የአለም ትልልቅ ካምፓኒዎች መፈልፈያ እና የብልፅግና ማሳያ መሆን ችላለች፡፡
የጥንቸልነትን ትርክት አራግፎ ነብርነትን ያስታጠቃቸው ስነልቦና መፈፀም፤ማሳካት፤መለወጥ፤ማደግ እንደሚችሉ ማሳያ ሆነ፡፡
አሁን ጥያቄው ኢትዮጵያን ማበልጸግ እንድንችል እኛስ ከዚህ ምን እንማር የሚለው ነው፡፡
መልሱ ቀላል ነው….
እኛ ኢትዮጵያውያን ከውጪ በመጣ ጠላት የታሪክ ትብታቦ ያልተዘወርን፤ የግዞት ቀንበር ያልተጫነብን፤ የአሸናፊነት ስነልቦና ዘወትር ያልተለየን ህዝቦች ነን፡፡ መሬታችን ለም እና ሰፊ፤ ህዝባችን እልፍ፤ተፈጥሯችን ባለ ብዙ በረከት፤ ነፃነታችን ሽንፈት አልባ የሆነ፤ ግምባራችን ላይ ድል የተፃፈ አሸናፊዎች ነን፡፡
ረሀብ ቢወረን በእጆቻችን ስንፍና፤ጥማት ቢያቃጥለን በማንቀላፋታችን፤ ስንዴ ቢሰፈርልን ትጋት በማጣታች እንጂ ወደ ብልፅግና ለመስፈንጠር ጥሪት አልባዎች ሆነን አይደለም፡፡
ያለንን ውድ ስጦታ መንዝረን ወደ ሀብትነት ቀይረን ዛሬ ብንነሳ ቁንጮ መሆን የምንችል፤ ብንሰራ እና ብንተጋ ተፈጥሮ ፊቷን የማታዞርብን፤ ከኋላ የሚጎትት የጭቆና ቀንበር የሌለብን፤ በህብረት ስንቆም አሸናፊዎች መሆን የምንችል እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
ኢትዮጵያን ለማበልፀግ የአሸናፊነት፤የፈፃሚነት፤የጨራሽነት፤የድል አድራጊነት፤የሰርቶ አሳይነት እና በህብረት ድል አድራጊነት ስነልቦናን አጎልብተን ወደ ብልፅግና ባቡር መሳፈር ይጠበቅብናል፡፡ እንንቃ! ትኩረታችን በከንቱ ሳይባክን፤አቅማችን ሳይዝል ታካችነት እና አሳባቢነትን ወደ ጎን ትተን ለታላቅ ሀገር ግንባታ እንሰለፍ፡፡
ሀገር አንድ በሆኑ ህዝቦች እንጂ በተከፋፈሉ አትገነባምና ህብረታችን ይጠንክር፤ሀገር በአሸናፊነት ስነልቦና እንጂ በሰበብ አብዢነት እሳቤ አትበለፅግምና ምክንያት ደርዳሪነትን እንተው፡፡ሀገር ለህዝቡ አንድ የውሀ ጉድጓድ መቆፈር በሚችል እንጂ በጎጥ እሳቤ ንትርክ ሲፈትል ውሎ በሚያድር መፍትሄ አልባ ፖለቲከኛ መገንባት አትችልምና የሴራ ፖለቲካን ገፍተን ወደ ሀሳብ እንመለስ፡፡ ድህነትን ስንረገም መዋልም ወደ ብልፅግና አያሻግርም እና ትኩረታችን ብልፅግና ይሁን፡፡

ምላሽ ይስጡ