ያለፈው ዓመት ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች የተከናወኑበት መሆኑ ተገለፀ

ያለፈው ዓመት ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች የተከናወኑበት መሆኑ ተገለፀ

  • Post comments:0 Comments

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ አመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ጉባኤ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚገኘው የስብስባ አዳራሽ ተካሄደ፡፡የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያለፈው አመት ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮችን በማከናወን ስኬት ያስመዘገብንበት ዓመት ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሰላምን ለማምጣትና የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነትን ለመፍታት ባደረጉት ጥረት የኖቤል ሽልማት የተሸለሙበት ዓመት መሆኑ አንዱ ስኬት መሆኑን በመግለጽ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሁኔታ በመቀየር የሃገራችንን ስም በአለም መድረክ ማስጠራት የተቻለበት ነው ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ አያይዘውም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የነበሩ የአሰራር ችግሮችን በመፍታት እና የግድቡን ግንባታ በማፋጠን በዲፕሎማሲ ረገድ የሃገራችንን ክብር እና ጥቅም ለማንም አሳልፈን የማንሰጥ መሆናችንን ለአለም ያስመሰከርንበትና የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በድል የተወጣንበት ዓመት መሆኑም ሌላ እንደ አገር የተመዘገበ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አዲስ የምርጫ አዋጅ በማፅደቅና ምርጫ ቦርድን ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ በማደረጀት ከዴሞክራሲ ግንባታ አንፃር የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የሲዳም ክልልነትን ጥያቄ ለማስተናገድ ስኬታማ የሆነ የህዝበ ውሳኔ ምርጫን ለማካሄድ የተቻለበት ነበር ብለዋል፡፡ በዓመቱ በተደረገው ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ፖሊሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እና ችግሮቻቸውን በመካፈል እንዲሁም በሃገራቸው ጉዳይ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ አለኝታ እና ስሜትን በመፍጠር ውጤታማ ስራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡ኮሮናን በመከላከል ረገድ ቀድሞ ለመከላከል በተሰራው ስራ አፋጠኝ የጤና ተቋማትን መገንባት መቻሉን የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ የመከላከያ እና የማከሚያ ቁሶችን ከአገር አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች የማዳረስ ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡ ዓመቱ በኩታ ገጠም እርሻ ለሃገራችን የግብርና ልማት ተስፋ ሰጪ ውጤት የተገኘበት፣ ካለፉት አመታት በተሻለ የውጭ ንግድ ገቢ የታየበት፣ 5 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማድረግ የታሰበው እቅድ የተሳካበት፣ ሃገራችን ለቀጣይ 10 አመታት የምትመራበት ፍኖተ ብልፅግና የተነደፈበትና በጥቅሉ በርካታ ታሪካዊ ድሎች እና ስኬቶች የተስተናገደበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply