የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የአንደኛ ሩብ አመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በማድረግ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በሩብ አመቱ የተፈፀሙ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በመገምገም ላይ ነው።
የተመረጡ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ተወካዩች የሩብ አመት አፈፃፀማቸው ምን እንደሚመስል ሪፖርት እያቀረቡ ሲሆን ከፓርቲው ዋና ፅ/ቤት ጋር በተናበበ መልኩ የተቀናጀ የህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት የሚያስችል አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የስራ አፈፃፀም ግምገማውን በንግግር የከፈቱት የፓርቲያችን የህዝብ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሳዳት ነሻ ብልፅግና ፓርቲን ጊዜውን የዋጀ የህዝብ ግንኙነት ውጤት ባለቤት ለማድረግ ኮርፖሬት የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ፣የህዝብ ግንኙነት እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን አካሄድ መቀየስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህም ጠንካራ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ ለመግባት በዘርፉ በኩል ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች እቅዱን በሚገባ በመረዳት ለስኬታማነቱ አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
በውይይቱ ቀናት የሚቀመጡ አቅጣጫዎችንም በአስቸኳይ ወደ ተግባር በማስገባት ሊታይ የሚችል ለውጥ በፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ሊመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውጤቱም የብልፅግና ፓርቲ መሰረታዊ የሆኑ ፖሊሲዎች፣መመሪያዎች እንዲሁም እቅዶች ወደ ህዝቡ ደርሰው የፓርቲያችንን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መገንባት እና ለቀጣይ የልማት፣የሰላም፣የዴሞክራሲ እና የብልፅግና እቅዶች ስኬት የህዝብ ግንኙነት ስራችን ጉልበት መፍጠር መቻል እንዳለበት አስገንዝበዋል።