ወንድም በወንድሙ ላይ የጨከነበትን፣ አብረን የኖርን ቀርቶ አብረን የዋልን በማይመስል መልኩ የተጋጨንባቸውን፣ በረባው ባልረባው የሰው ሕይወት የተቀጠፈባቸውን፣ ዒላማ እንጂ ዓላማ በሌላቸው ሰዎች የወገኖቻችን ደም በከንቱ የፈሰሰባቸውን ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ዞር ብለን ስናይ ልባችን በኀዘን ይሰበራል። እንደ ትውልድም ሐፍረት ይሰማናል፡፡
በሰሜኑና በምዕራቡ የሀገራችን ክፍሎች ጦርነቶችና ግጭቶች ያስከፈሉንን የሰው ሕይወትና የወደመውን የሀገር ሀብት ስናስብ ዓይኖቻችን ብቻ ሳይሆኑ ነፍሶቻችንም ያነባሉ።
በአንድ ወቅት በምሥራቁና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ተከሥቶ የነበረው ጥፋት ያደረሰው ጉዳትና ሰቆቃም የሚረሳ አይደለም። እያነባንም ቢሆን ግን እናመሰግናለን፡፡ ከሆነብን የተደረገልን ይበልጣልና፡፡
አንገቷን ለመስበርና ወገቧን ለማጉበጥ የወረደባትን መዓት ሁሉ ችላ፣ ኀዘኗን በሆዷ፣ ፈተናዋን በክንዷ ተሸክማ አልፋ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም በጽናት መቀጠሏና አቅጣጫዋን ሳትስት በመንገዷ ላይ መገሥገሷ በርግጥ አስደናቂ ምሥጢር ነው።
በጥፋት ውስጥ ልማትን፣ በኀዘን ውስጥ መጽናናትን፣ በችግር ውስጥ በረከትን፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን እያበራ የታደገንና ለሀገራችን ድጋፍና መከታ የሆነን የኢትዮጵያ አምላክ ነው፡፡ ይሄንን ጥላ ከለላ፣ አምባ መከታ፣ ጋሻ መሸሻ የሆነ አምላክ ማመስገን የኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነት ዜማ መሆን ይገባዋል፡፡
ዶ/ር ዐብይ አህመድ