የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ መድረክ መካሄድ ጀመረ
በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ መድረክ በአዳማ መካሄድ መጀመሩን የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
በፓርቲው የወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝደንትና የጽ/ቤት ኃላፊ ወጣት አክሊሉ ታደሰ የውይይት መድረኩ በሶስት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸው የጉባኤ ውሳኔዎችን አስመልክቶ የወጣቶች መድረክ አፈፃፀም መገምገም፣የምግቤን ከጓሮዬ የደረሰበትን ደረጃ መገምገም እንዲሁም በቅርቡ ለሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ 1ኛ ጉባኤን በተመለከተ የውይይት መነሻ አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ኃላፊው አያይዞም በፓርቲ የጉባኤ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን ዙሪያ ማወያየት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከ3 ሚሊዬን በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸው ይህ ሀገራዊ መድረክ ሃገራችን አሁን ባለችበት ዘርፈ ብዙ ጫናዎች ውስጥ ባለችበት የተካሄደ መድረክ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ወጣቱ ያለውን ጥያቄ በሚገባ ለመረዳት ያስቻለ ነበር ብለዋል፡፡
በፓርቲው ውሳኔዎች ላይ ወጣቶች በራሳቸው አደረጃጀት ውይይት እንዲያደርጉ መደረጉን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ወጣት አክሊሉ ወጣቶቹ በስፋት መፈታት አለባቸው ብለው ያነሷቸውን የኢኮኖሚ ጥያቄዎች፣የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና መሰል ጥያቄዎች እንዲፈቱ የሊጉ መዋቅር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የወጣት ሊጉ ስራ አስፈጻሚ አባላት የወጣቶች የውይይት መድረክን ለመምራት በየተመደቡበት ክልል የነበረውን ጠንካራና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡