ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ግሽበቱ…

ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ግሽበቱ…

  • Post comments:0 Comments

ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ግሽበቱ በቂ ትኩረት በመስጠት ህዝብ ለሚያነሳው እሮሮ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት የግድ ያስፈልጋል፤ይህ ሳይሆን ቀርቶ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ በዚህ ከቀጠለ ከአሸባሪዎቹ ህወኃትና ሸኔ በላይ የህልውናችን አደጋ፣የደህንነትና የጸጥታ ስጋት የመሆን አዝማማሚያ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በልኩ መረዳት ይኖርብናል፡፡

የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ከዳር እስከ ዳር ለመላው ኢትዮጵያዊያንን መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነ፣የዜጎችን ኑሮ በብርቱ እየተፈታተኑ የሚገኙ በመሆናቸውና ከኢኮኖሚያዊ ችግርነት አልፈው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይፈጥሩ ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጣቸው የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በቅርቡ ከህዝብ ጋር በነበራቸው ህዝባዊ ውይይት አንስተዋል፡፡

መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ኩታ ገጠም ግብርናን፤ የቆላ ስንዴን ፤የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት፤ የአረንጓዴ አሻራን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።  ምርት ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ አይሆንምና ዋናው ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ብልሹው የግብይት ስርዓትን በአግባቡ ማረምና ተገቢውን ክትትል ማድረግ፤ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ደላሎችን ከገበያው ማስወጣት፤ በቂ ምርት እያለ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ በየቦታው የሚከዝኑ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ፣የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን በሕግ ስርዓት ማስያዝና በህግ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም ይሄ ሁሉ ችግር በመንግስት የተናጠል ጥረት ብቻ ሊፈታ ስለማይችል ልዩ ልዩ ሲቪክ ማህበራት፣ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሸማቾች ማህበራት፣የፀጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

Leave a Reply