ከውጭ ተጽእኖ መላቀቅ እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ኢኮኖሚያችንን ማሳደግና መበልጸግ ስንችል ነው፡፡ የውስጥ ችግሮቻችንን በራሳችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት መፍታት የሚቻለው በውስጥ አቅማችን ጎልብተን ስንገኝ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡
ጠላት የሚፈታተን የውስጥ አንድነታችን ሲላላ፣ኢኮኖሚያዊ አቅማችን የደከመ ሲሆን እና የእርስ በእርስ ትስስራችን መድከሙን ሲታዘብ ነው፤ስለሆነም በሁለንተናዊ መልኩ አቅማችን ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡
አገራዊ ልማት ላይ ትኩረት አደርገን በመስራት ለመጪው ትውልድ ራሷን የቻለች የማንንም እገዛና ጣልቃ ገብነት የማትሻ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስ ያስችለናል፡፡ ኢኮኖሚ ለሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ የውስጥ ኢኮኖሚያችን ካደገ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል፣ስራ አጥነት ይቀንሳል፣ፖለቲካዊ መረጋጋት ይመጣል፣የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል…..፡፡
ከአገራት ጋር የምናደርገው ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ በኢኮኖሚም የምናካሂዳቸው የትብብር ግንኙነቶችን ማስፋትና ማጠናከር ይገባናል፣እንደ አገርም ቢሆን ለጸብ ምንጭ የሆኑ ልዩነቶቻችንን አስወግደን ሁለንተናዊ ትብብራችንን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡