“እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ“ መሆን ይገባናል፤ /በሚራክል እውነቱ/

“እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ“ መሆን ይገባናል፤ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
አንድ አገር እንደ አገር እንዲቀጥል ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ሰላም ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታል። ሰላም ካለ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት ተምሮ መለወጥ እና ያሰቡትን ሁሉ ማሳካት ብዙ ከባድ አይሆንም። ነገር ግን ሰላም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከተናጋ ይህ ሁሉ ነገር እንዳልነበር ከመሆኑም በላይ አገርም ህልውናዋን ጠብቃ ልትቀጥል የምትችልበት ሁኔታ በጣም ጠባብ ይሆናል።
 
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም እየታየና እየተሰማ ያለው ነገር እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ የቀደመውን የመተሳሰብ፣ አብሮ የመኖርና የመደማመጥ ባህላችንን የሚያጠፋ፣ እንደ አገርና ህዝብ ወደኋላ የሚጎትተን መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ ችግር እንድንወጣ “እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ“ ልንሆን እንደሚገባም ብዙዎች እየመከሩ ይገኛሉ።
 
አሁን እየታሰበ ያለው አገራዊ የምክክር መድረክ እንደ አገር ብዙ የታሰበበት፣ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጸድቆ ብዙ ታምኖበት የቀረበ፣ ብዙ ተስፋም የተጣለበት ነው። አሁን ለመጣው አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊውን ትኩረት መስጠትና ተገቢውን እገዛ ማድረግ የምንችል ከሆነ ውጤታማ መሆኑ አይቀርም።
 
የሚያጨቃጭቁንን እንደ አገርና ህዝብ አንድ ሆነን እንዳንቀጥል እንቅፋት የሆኑን ነገሮች ላይ መመካከሩ በጣም ጠቀሜታ እንዳለው ለማንም ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያለመግባባታችን መነሻ እየሆኑ ካስቸገሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሰንደቅ አላማ ነው። ይህንን ጉዳይ ህዝቡ ምን ይላል? ውስጡ ምንድን ነው ያለው? የሚለውን እስከ ወረዳ ድረስ ወርዶ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግና የህዝቡን ስሜት መረዳትና ማወቅ፣ በተገኘው ውጤት መሰረትም ወደ መፍትሔና ምላሽ መምጣት ተገቢ ብቻም ሳይሆን ግዴታም ነው።
 
ሌላው የብዙዎች የውይይት አጀንዳ ሆኖ የምናገኘው ጉዳይ አንቀጽ 39 ነው። ይህም ቢሆን ህገመንግስታዊ አሰራርና አካሄድ ያለው እንደ አገር በውይይት ወደ መግባባት መምጣት የሚቻልበት ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ ይኖርብናል።
 
የክልሎችን የመዋቅር ጥያቄን መመለስም ሌላ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። የክልል እንሁን ጥያዎች እዛና እዚህ በተነሱ ቁጥር መልስ በመስጠታችን እንደ አገር የምናገኘው ጥቅምና የምናጣው ነገር ምንድን ነው? የሚለውን ጊዜ ሰጥቶ መፈተሽ ብልህነት ነው። በመሆኑም ህዝብ ያመነበትንና የተቀበለውን ወደተግባር እየቀየሩ ያላመነበትን ደግሞ ወደጎን እየተው ወደሰላማዊ አደረጃጀታችን መግባት ያስፈልገናል።
 
እነዚህንና መሰል ተግዳሮቶችን ምላሽ መስጠት ያስችላል የተባለ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል።ገና ወደ ስራ ከመገባቱ አንዳንድ ተግዳሮቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ዋናው ነገር በየጊዜው ለሚገጥሙን ፈተናዎች ሳንንበረከክ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ መደገፍ እና ተመካክረን ችግሮቻችንን መፍታት ትልቅነት ነው።
 
እንደ አገር ለችግሮቻችን መፍትሔ የምናፈላልግበት ባህላዊ እሴቶቻችን ቢኖሩም የምንሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ከመምጣቱም ባሻገር አንዳንድ እኛ እናውቅላችኋለን ባዮች የሚፈጥሩብን ጫና ሌላው ችግር ሆኖ ቆይቷል።
 
እነዚህን አካላት ወደጎን ትተን የራሳችንን ባህላዊ እሴቶቻችንን ማጎልበት የምንችል ከሆነ ለበርካታ ችግሮች ምላሽ ማግኘት ከመቻላችን አልፈን ለብሔራዊ ምክክሩ ትልቅ አቅምና ጉልበት ይፈጥርልናል ብዬ አስባለሁ።አዕምሮው በተንኮል የተሞላ አካል ከብሔራዊ ምክክሩም በኋላ ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።ለዚህ ደግሞ ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ማስተዋልን መላበስና ሰከን ብሎ ማሰብ ተገቢነት አለው።
 
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስራውን ቢጀምርም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል።ፈተናዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ሊቀጥሉ ይችላሉ። በመካከል የተለየ ፍላጎት ያላቸው አካላት ህዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ ሐሳብ ሊሰነዝሩ ይችላሉ።
 
መገናኛ ብዙሐን የኮሚሽኑን ተግባርና አገራዊ ኃላፊነት ለህዝቡ በሚገባ ያለማሳወቅ ችግሮች ሊከሰት ይችላል።በመሆኑም በተረጋጋና በሰከነ መንገድ ነገሮችን ለውይይት ማቅረብና ህዝቡ የመጨረሻ ዳኛ እንዲሆን መወሰን ተገቢ ነው እላለሁ።

Leave a Reply