ሰላም በየትኛውም ዓለም ስለተፈለገ ብቻ የሚገኝ ማህበራዊ ሀብት አይደለም፤እንዳያያዛችን ሁኔታ የሚወሰን እንጂ፡በአግባቡና በጥንቃቄ ከያዝነው ከእኛው አልፎ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚቻል ሲሆን በውሃ ቀጠነ ከመግባባትና ነገሮችን በሰከነ መንገድ እንደ ሰለጠነ ዜጋ በውይይት መፍታት የማንችል ከሆነ ግን ሰላማችንን አጥተን በሰከንዶች ሽርፍራፊ ወደ ለየለት ግጭትና ትርምስ ውስጥ ሊያስገባን የሚችልበትም አጋጣሚ አለ፤ለዚህም ነው የሰላም ዋጋው ስንት ነው? የሚባለው፡፡
ሰላም ከየትም የሚመጣ ቁስ አይደለም፤ ከሁላችንም መዳፍ የሚገኝ የሁላችንም እኩል ሀላፊነት የሚፈልግ ልዩ ሀይል ያለው ማህበራዊ ሀብታችን ነው፡፡በአንዳንድ ሀገራትን የሚኖሩ ህዝቦች ለምሳሌ በቅርቡ ጎረቤት አገር ሱዳንን እንኳ ወስደን ብንመለከት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ህዝቡ የሰላም አየር መተንፈስ አቅቶት ሲቸገር ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክቷል፡፡
በእኛም ሀገር ቢሆን መልካም መልካም ስራዎችን ከማበረታታት ይልቅ ሰበቦችን እየፈለጉ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚፈልጉ እንቅፍ አጥተው የሚሰሩ ሀይሎች እንዳሉ እሙን ነው፡፡
የህዝብና የሀገር ሰላም ማጣት ለማን በጄ? ችግሮች እንኳ ሲኖሩ ተቀራርበን ለችግሮቹ መፍትሔ ማምጣት ለመንግስት ወይም ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚተው ሳይሆን እያንዳንዳችን የመፍትሔው አንድ አካል እንደሆን ልናስብና የጋራ ሰላማችንን በተልካሻ ምክንያት እንዳናጣው ልንረባረብ ይገባል፡፡
ሰላምን መጠበቅም ይሁን ማስጠበቅ ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ተግባር አይደለም፡፡ ከወጣቶች፣ከምሁራን፣ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ከተማሪዎች፣ከመምህራን፣ከጸጥታ ሀይሉ፣ ከግልና ከመንግስት ሚዲያዎች…ብቻ ሰላምን የሚሻ ሁሉ በጋራ ሊጠብቁትና ሊያስጠብቁት ይገባል፡፡