አገሩን የሚወድ ሰው ሁሉ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ማለት ሁሉንም ጨፍልቆ አንድ ማድረግና በአንድ ሃሳብ እንዲስማማ ማድረግ ሳይሆን መሠረታዊ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አተያይ መያዝን የሚመለከት ነው፡፡
ምክንያቱም በአንድ አገር ወይም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ስለማይኖር ሕዝብም በሁሉም ነገር ላይ ይግባባል ማለት አይቻልም። ሆኖም ልዩነቱን አቻችሎ ለድርድር በማይቀርቡ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለአገር በሚጠቅም መልኩ በጋራ መስራት የግድ አስፈላጊ ነው።
ከአገር እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም አንጻር ለድርድር የማይቀርቡ ነጥቦችን በመለየት የጋራ እስቤና መግባባት መያዝ የሚገባን ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መወያየት ያስፈልጋል፡፡
ለአብነትም፣ በመሰረታዊነት ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ላይ መግባባት ካልተቻለ አብሮ መኖርም ሆነ እንደ አገር የሚታሰበውን ብልጽግና ማምጣት ያስቸግራል፡፡
ከሕገ መንግሥቱ በተጓዳኝም በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አስፈላጊ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ላይም ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መቻል ሊፈጠሩ ከሚችሉ አላስፈላጊ ክስተቶች ይታደጋል፡፡
እንደ አገር አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ መፍጠር ያስፈለገበት አንደኛው ምክንያት ዋና ዋና በተባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማለትም በህገ መንግስቱ፣ በሰንደቅ ዓላማና በመሳሰሉት አንኳር ጉዳዮች ላይ አብዛኛው ማህበረሰብ ያመነበት እንዲሆን በማስቻል ከፋፋይ ሀሳቦችን በገንቢና ሊያቀራርቡ በሚችሉት በመተካት እንደ አገር ሰላም መፍጠርና አገራዊ ብልጽግናን በተሻለ ፍጥነት እንዲረጋገጥ ማስቻል ነው፡፡
ይደረጋል የተባለው ይህ አገራዊ የምክክር መድረክ በህዝቡ እና በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል የጋራ መግባባት ማስፈንን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በህዝብ እንደራሴዎች በኩል አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ አካላት ጋር መደራደር ማለት እንዳልሆነ መጠቀሱ የሚታወስ ነው፡፡
የለውጡ አመራር ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አገራዊ የምክክር መድረክ እንዲፈጠር በዋናነት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ እንደ መሪ ፓርቲም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደረጃ፣ በተለያዩ ሲቪክ ማህበራትም አካታች አገራዊ ምክክር ለአገራችን በጣም አስፈላጊ እንደሆን ሲነሳ ቆይቷል፡፡
ስለሆነም ይህን አካታች አገራዊ ምክክር በታሰበው ልክ መፈፀም ከተቻለና ህዝቡም ይህ እንዲሆን ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ከቻለ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ፈር ማስያዝ ይቻላል፡፡
በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የበለጠ ማጠናከር ያስችላል፡፡
አገራዊ ምክክሩን ለማስጀመር ነጻ እና ገለልተኛ ተቋም ስለሚያስፈልግ ምክክሩን የሚያስተባብር ኮሚሽን ተቋቁሞና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
የጋራ ማንነትንና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እኩል ይዞ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ከመፍታት አኳያ አካታች አገራዊ ምክክር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡