የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት መረጋጋትን፣ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ኢኮኖሚን ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጠን መስራት፣ አንድነታችንንና የእርስ በእርስ ትብብራችንን ማጠናከር ፣ወንድማማችነታችንን በማጎልበት ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በጽኑ መሰረት ላይ እንድትገነባ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
ከውጭ ተጽእኖ መላቀቅ እና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ኢኮኖሚያችንን ማሳደግና መበልጸግ ስንችል ነው፡፡ የውስጥ ችግሮቻችንን በራሳችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት መፍታት የሚቻለው በውስጥ አቅማችን ጎልብተን ስንገኝ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡
ጠላት የሚፈታተን የውስጥ አንድነታችን ሲላላ፣ኢኮኖሚያዊ አቅማችን የደከመ ሲሆን እና የእርስ በእርስ ትስስራችን መድከሙን ሲታዘብ ነው፤ስለሆነም በሁለንተናዊ መልኩ አቅማችን ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡
አገራዊ ልማት ላይ ትኩረት አደርገን በመስራት ለመጪው ትውልድ ራሷን የቻለች የማንንም እገዛና ጣልቃ ገብነት የማትሻ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስ ያስችለናል፡፡ኢኮኖሚ ለሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡የውስጥ ኢኮኖሚያችን ካደገ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል፣ስራ አጥነት ይቀንሳል፣ፖለቲካዊ መረጋጋት ይመጣል፣የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል…..፡፡
ከአገራት ጋር የምናደርገው ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዳለ ሆኖ በኢኮኖሚም የምናካሂዳቸው የትብብር ግንኙነቶችን ማስፋትና ማጠናከር ይገባናል፣እንደ አገርም ቢሆን ለጸብ ምንጭ የሆኑ ልዩነቶቻችንን አስወግደን ሁለንተናዊ ትብብራችንን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡
ሁለንተናዊ ነጻነታችንን ማወጅ የምንችለው ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት ስንችል በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ፊታችንን ወደ ልማት ስራዎች ማዞር ይኖርብናል፡፡አገራዊ ኢኮኖሚ ማደግ የሚችለው ለልማት በምንሰጠው ትኩረትና ትግበራ ላይ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡
አገራችን ወደ ብልጽግና ማማ ለመውጣት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን ለማንም የተደበቀ አይደለም። በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ወደ ከፍታው ማማ የሚያሻግሩንን መሰላሎች መስራት ከጀመርን ሰንበትበት ብለናል።
መንገዳችን መደመር መዳረሻችን ብልጽግና ነው ስንል በምክንያት ነው፤ወደ ብልጽግና የሚወስደውን ጥርጊያ መንገድ ጀምረናል፡፡ሆኖም ግን ከምንፈልገው ከፍታ ላይ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን በትዕግስትና በጽናት ማለፍ እንዳለብን ሳይታለም የተፈታ ነው።
ማንኛውም ውጤት እንዲሁ በዋዛ የመጣ እንዳልሆነ መረዳት፣ ከፊት ለፊታችን ሊገጥሙን የሚችሉ ፈተናዎች እንዳሉና ፈተናዎችን በብስለትና በሰከነ መንገድ ለመፍታት ራሳችንን ዝግጁ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
አገራዊ ዕድገትና ብልጽግና በከፍታና ዝቅታ፣በውጣ ውረዶች የተሞላ፣ጋሬጣ የበዛበትና በእልህ አስጨራሽ እንቅፋቶች የታጀበ በመሆኑ አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም።
ምዕራባዊያን ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የደረሱት በዕድል ሳይሆን ከበርካታ ጥረትና አልሸነፍ ባይነት በኋላ፣ ከድህነት ለመውጣት ባሳዩት ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ፣በቁጭትና በትጋት ተነሳስተውና የሥራ ባህላቸውን ለውጠው መስራት በመቻላቸው ነው። አንድ ሆነው መጪውን ትውልድ አስበው በመስራታቸው ጭምር ነው። ዛሬ ለምንወዳት ኢትዮጵያችን የሚያስፈልጋትም ይሄው ነው።
የስራ ባህላችንን መለወጥ፣በሚገጥሙን ፈተናዎች እጅ አለመስጠትና ተስፋ አለመቁረጥ፣እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችን መሻገር፣ብዙ እሾህና አሜኬላዎችን ነቃቅሎ ማለፍ፣ሌት ተቀን እጃችን እስኪሻክር መስራትን ይጠይቃል።
ሁሉም በእልህና በወኔ ከሰራና በውስጥም በውጪም ያለው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለውድ አገራቸው መለወጥ እያሳዩት ያለውን መተባበር አጠናክረው ከቀጠሉ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከብልጽግናው ማማ ላይ መድረስ የማንችልበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። የወቅቱ ትግላችን ይሄንኑ ለማረጋገጥ ነው።