ኢትዮጵያ ታሸንፋለች !!
***********************************************************************
አገርን ለመደገፍ የተለያየ መንገድን መከተል ግድ ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ ሠላማዊ ሰልፍ ነው፤ ይህም ሁለት መስመሮችን ይይዛል። የመጀመሪያው ጠላትን በተቃውሞ ማውገዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው በመኖርና በመተግበር ለአገር መቆምን ማሳየት ነው። ዛሬ ደግሞ ይህ ነገር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጊዜ እንደሆነ በደንብ ይታመናል። ሰዎችም ከውጪም ከውስጥም የሚነሳውን የጥላቻ ስብከት ለመቃወም በየፊናቸው የወጡት ለዚህ ነው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ብዙም ሰላም ያልሰጣቸው አገራት፤ከአሸባሪው ህወኃት የጥፋት መንገድን ጋር ተቆራኝተዋል። በመደገፍም የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት፤ ከዛም ባለፈ ሕልውናዋን ስጋት ውስጥ በሚጨምር የተናበበ የጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገኛሉ።
አሜሪካ የአገር ነቀርሳ የሆነውን የአሸባሪው ህወኃት ተፈጥሯዊ ሞት ለመቀልበስ በብዙ መልኩ ከቡድኑ ጋር ሰልፈኛ ሆናለች። የቡድኑን የሽብር ተግባሮች እንዳላየ ከማየት ጀምሮ በመንግሥት ላይ ያልተገቡ ጫናዎችና ማስፈራሪያዎች እስከ ማሰማት ድረስ የሚደርሱ ተግባራትን ታከናውናለች።
መንግሥት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን በአሸባሪው ቡድን ላይ ሲወስድ ከፍ ባሉ ጩኸቶች ዓለም አቀፍ መድረኮችን ማጣበብ፤ ቡድኑ ስኬታማ የሆነ ሲመስላት ደግሞ ዝምታን በመምረጥ ግልጽ የሆነ ድጋፏን ለአሸባሪው ቡድን በመስጠት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ የሽብር ተግባር ጋር ያላትን አጋርነት ታሳያለች።
ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወኃት ጋር የገባችበት ጦርነት ፈልጋው ሳይሆን ተገዳ እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። ቡድኑ ወደ ጦርነት እንዳይገባ ብቻ ሳይሆን በሠላማዊ መንገድ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ እንዲሰራ በብዙ መንገድ ተለምኗል።
መንግሥት ለጀመረው የልማት እና የብልጽግና ጎዳና እንቅፋት እንዳይሆንም ተማጽኖ ጭምር ተደርጎለት እንደነበረ ይታወሳል። ነገር ግን ቡድኑ ከተዛባ የኃይል አሰላለፍ ስሌት ባለፈ እብሪት እና ከምዕራባውያኑ እያገኘ ባለው አይዞህ ባይነት አገርና ሕዝብን ስጋት ውስጥ በሚጨምር የሽብር ተግባር ውስጥ ተዘፍቋል።
አሁን ኢትዮጵያዊያን እያሳለፉት ያለው ፈተና እና ትግል በታሪኩ ተሻግሮ ከመጣቸው የሚያንስ እንጂ የሚበልጥ ባለመሆኑ አሸናፊነቱ አያጠያይቅም።