You are currently viewing ከከፍታው ሆነን እንጠብቃቸዋለን! /በማራኪ አያሌው/

ከከፍታው ሆነን እንጠብቃቸዋለን! /በማራኪ አያሌው/

  • Post comments:0 Comments
ከከፍታው ሆነን እንጠብቃቸዋለን!
በማራኪ አያሌው
አሜሪካ ቡራኬዋን ያላገኘ መንግስት እና ሀገርን ድምጥማጡን ለማጥፋት የማትገባበት የለም፡፡ የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና መለኪያ አድርጋ ራሷን የሚታቀርበው አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት ከስልጣን አውርዳ፤ የራሷን ፍላጎት በሚፈጽም ተላላኪ መንግስት ለመተካት የማትቆፍረው ጉድጓድ፤ የማትቧጥጠው ተራራ አይኖርም፡፡ የሚጨፈጨፉት ህጻናት እና ንጹሓን፤ የሚደፈሩት ሴቶች፤ የሚወድመው ንብረት…ወዘተ ለዚች አገር ምኗም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ የሚሆነው በገዛ ሀገሯ፤ በገዛ ወገኗ ላይ ሳይሆን በሌሎች ሀገራት ሰማይ ስር በመሆኑ፡፡
ቆሌዋ ያልወደደው ወይም ለእሷ የማይታዘዝ መንግስት እና ሀገር አለ ብላ ከገመተች ያለስም ስም በመስጠት በቀጥታ ወረራ ታካሄዳለች፡፡ በኢራቅ ሳዳም ሁሴን “ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ታጥቋልና አለምን ሊያጠፋት ነው” ብላ ስም በመስጠት ወረራ በማካሄድ ኢራቅን ዶጋመድ እንዳደረጋቻት ማለት ነው፡፡ ከወራረው በኋላ ግን የተባለው ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ በኢራቅ ምድር ሊገኝ እንዳልተቻለ ዓይኗን በጨው አጥባ ለዓለም አበሰረች፡፡
በቀጥታ ወረራ ለመፈጸም ካልተሳካላት ደግሞ በተጨባጭ የሌለ ምክንያት ትፈጥርና ከሀገር ውስጥ ከመንግስት ጋር ቁርሾ ያለውን አካል በማደራጀት እሳቱን ትለኩሳለች፡፡ ከመጋረጃ ጀርባ ለአንደኛው ወገን ቤንዚል ለሌላኛው ተፋላሚ ደግሞ ጭድ ታቀብላለች፡፡ በ1994 ብቻ በውስጥ ጦርነት ሲታመሱ ከነበሩ 50 ሀገራት ውስጥ በ45 ሀገራት አሜሪካ አንደኛውን ወገን የማስታጠቅ ስራ መስራቷን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡
እቅዷ እየሰመረ ሲሄድ ብቅ ትልና የመግለጫ ጋጋት ታዘንባለች፤ አለፍ ሲልም “እናደራደራቸው” የሚል ሽንግላ ታቀርባለች፡፡ አለፈ ሲል ደግሞ የሽግግር መንግስት አማራጭ ይዛ ብቅ ትላለች፡፡ በለስ ከቀናት የሷን ፍላጎት የሚፈጽም አካል መንግስት አድርጋ ትሾማለች፡፡ ካልሆነ ደግሞ በሰብዓዊ መብት እና እርዳታ ስም የሰላም አስከባሪ ሐይል በዚያች ሀገር መሰማራት አለበት ብላ ትደመድምና የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት እንዲያከትም ታደርጋለች፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የተለኮሰው እሳት ንጹሐንን ይለበልባል፡፡ አሜሪካ ደግሞ ሁኔታውን በሩቅ እንደፊልም ትኮመኩመዋለች፡፡
ወዲህ ደግሞ የምትሰራው እኩይ ተግባሯ እንዳይታወቅባት እና ተቃውሞ የሚያሰማውን አካል ጩኽቱን ለመቀማት በሚዲያዎቿ ፕሮፓጋንዳውን ታጦዘዋለች፡፡ ሚዲያዎቹ ያልተፈጠረን እንደተፈጠረ አድርገው ይቀባበሉታል፤ ተናበው አጅንዳውን ያራግቡታል፡፡ እነ ሲ ኤን ኤን፤ ሮይተርስ እና መሳሎቻቸው ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ እንዳደረጉት ማለት ነው፡፡ በአንዳች ተዓምር ሳሃራ በርሃ በግግር በረዶ፤ የሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች ደግሞ በርሃ ሆነው በአሸዋ ክምር እንደተሸፈኑ በማስመሰል ጉዳዩን ይዘግቡታል፡፡ አገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ዜጎች በአገራቸው ተስፋ እንዲቆርጡ፤ ግራ-መጋባት ውስጥ እንዲገቡ የስነ-ልቦና ጦርነት ይከፍቱበታል፡፡
ዜጎች አገር ለቀው እንዲወጡ መምከርም የዚች አገር የማንበርከኪያ እና አገራትን የማዋከቢያ አንድ መንገድ ነው፡፡ በዚህ የፕሮፓጋንዳ ማዕበል በርካቶች በርግገው ወይም በጥቅም ተታልለው አጅንዳውን ይገዙታል፤ እርምጀ ወደመውሰድ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ከነባራዊ ሀቁ በተቃራኒ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዚያ ሀገር ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ መሳል ይጀምራል፤ ቀጥሎም ወደ ማመን ይሸጋገራል፡፡
የሰሜን አፍርካ ፈርጥ የነበረችው ሊቢያን የፈረካከሰቻት፤ የስልጣኔ ማማ የነበረችውን ኢራቅንም የገነደሰቻት በዚሁ አኳኋን ነበር፡፡ እነ ሶሪያም ቢሆኑ ከገቡበት ማጥ ለመውጣት መንገድ ጠፍቷቸው ረመጥ ላይ ቆመው ባሉበት ወቅት አሜሪካና አጋሮቿ ግን ከዳር ተቀምጠው እሳቱን ይሞቃሉ፡፡ ያው ይህች ራሷን በሌላ አገራት ላይ አለቃ አድርጋ የሾመችው አገር እንዲህ ናት…ይሉንታ የማያውቃት፤ ዓለምን የእሷ የግል ስጦታዋ አድርጋ የምትቆጥር ናት፡፡
አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ጣልቃ የመግባት ሱስ ስለ ተጠናወታት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህንን የምታደርገው ግልጽ ዓለማ እና እቅድ ይዛ ነው፡፡ ይህም አንደኛው የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ስትል በየሀገራቱ የጦርነት እሳት ትለኩሳለች፤ ትደግፋለች፡፡ ይህንን በአህዝ ስንመለከት እ.አ.አ ከ2002 ወዲህ ብቻ በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ሽያጭ 2/3ኛውን የወጪ ንግድ ድርሻ ይሸፍናል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሐብትን ለመዝረፍ እና ለመመዝበር ሲሆን ይህም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ነዳጅ እና ማዕድን ያሉትን በቀጥታ ስትዘርፍ ቀሪውን ደግሞ በንግድ ተቋሞቿ አማካኝነት ትበዘብዛለች፡፡ በዚህ ረገድ የተፈጥሮ ሐብት ያላቸው ሀገራት እና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ወይም የገበያ አቅም ያለው ሀገር የጣልቃ ገብነት ሰለባ ናቸው ማለት ነው፡፡
ሌላኛው ምክንያት በቀጠናው የጂኦ-ፖለትካዊ ጥቅም እና የበላይነትን ለመያዝ የሚደረግ አሻጥር ነው፡፡ በአለም አቀፍ ፖለቲካ ስርዓት በተለይም በፉክክር ለሚያምኑ ሀገራት በስትራቴጂ ረገድ ጥቅም ያላቸውን ቦታዎች ለመያዝ የሚደረገው እሽቅድምድም እና አሻጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ብሉምበርግ ህዳር 03 ቀን 2014 ዓ.ም ይዞት የወጣው ዘገባ ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶችን ጠቅሶ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮችን መላክ እንዳለባት ያትታል፡፡ ይህም የዘፈን ዳርዳርታ…እንደሚባለው ወረራ ለመፈጸም ያላቸውን እቅድ ይፋ ያደረጉበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ አንድነት ጠንካራ ባልሆነባቸው ሀገራት እና ቀጠናዊ ተቋማት በልጠነከሩበት እንዲሁም ተላላኪ መንግስታት በሚገኙበት ቀጠናዎች ደግሞ የጣልቃ ገብነት ተጋላጭነት ይጨምራል፡፡
ከሁሉ ደግሞ በቀጥታ ወረራም ይሁን በእጀአዙር በአንድ ሀገር ውስጥ ጣልቃ ገብተው ያንን ሀገር እንዳልነበር አድርገው አፍርሰው፤ ሐብቱንም ዘርፈው ሲያበቁ “ያን ሀገር መውራራችን/መበጥበጣችን ስህተት ነበር” ይሉሃል፡፡ የቀድሞ የኤሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ “የሊቢያ ጦርነት የስልጣን ዘመኔ ትልቁ ስህትት ነበር” እንዳለው ማለት ነው፡፡
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት በአሸባሪው ህወሓት ታዝላ ዘው ብላ ለመግባት የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅማለች፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፤ ይህ ቅዠቷ ወደፊትም አይሳከም፡፡ ምክንያቱም እኛ የአድዋ ልጆች ነን! እኛ መቼም ቢሆን አብሮ ከማደግ፤ አብሮ ከመስራት፤ ከመተባበርና ከመገተጋገዝ ውጭ የሆነ ቁርኝት የማንቀበል ህዝቦች ነን፡፡ በነገራችን ላይ በአሜሪካ እና አጋሮቿ አሻጥር እና መሰሪነት የከሰሙ፤ የተፈረካከሱ፤ የወደሙ ሀገራት እንዳሉ ሁሉ እንደነ ራሽያ እና ኢራን ያሉት ሀገራት ደግሞ የውጭ ጠልቃ ገብነትን በጽኑ መመከት የቻሉ አብይ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
የሆነው ሆኖ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ካሃዲዎች በደገሱልን ጥፋት አማካኝነት ከዝቅታው ሲጠብቁን፤ እኛ በአንድነታችን ጸንተን ከከፍታው ሆነን እንጠብቃቸዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክሬ ታሪካችንና አይበገሬው ስነ-ልቦናችን ነው፡፡ አዎ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!

ምላሽ ይስጡ