ወቅታዊ የአገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያነሷቸው ሃሳቦች
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ጸሀፊ የሆኑት አቶ ክፍለማሪያም ሙሉጌታ በዓለም ላይ ብዙ አሸባሪ ድርጅቶችን ማየታቸውን ገልጸው እንደ ህወኃት አይነት እጅግ አስከፊና ጨፍጫፊ የሽብር ቡድን ግን አይቼ አላውቅም ሲሉ ተናግረዋል፤
አቶ ክፍለማሪያም አያይዘውም ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትንና አቅመ ደካሞችን ወደ ጦርነት እያሰለፈ የሚገኘው አሸባሪው የህወኃት ቡድን በእምነት ተቋማት ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋት በርግጥም ከምስረታው ጀምሮ ለጥፋት የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
አቶ ፈይሰል አብዱላዚዝ ከኦዴፓ በበኩላቸው አሸባሪው የህወኃት ቡድን እስካሁን በምን ምክንያት ሊቆይ እንደቻለ ግልጽ አይደለም ምክንያቱም ጦርነቱ በተጀመረ አካባቢ መቀሌ ለመግባት ሶስት ሳምንት ብቻ የወሰደበት ሰራዊታችን ከተማዋን ለቆ ከወጣ በኋላ ግን እየተደረገ ያለው ጦርነት የዘገዬ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልል ህዝቦች ላይ እያደረሰ ያለው ጭፍጨፋና እንግልት በዓለም አቀፍ የወንጀል ህግ የሚያስጠይቅ ነው ያሉት የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው ይህንን አሸባሪ ቡድን በአጭር ጊዜ ለማስወገድ እየተደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ መንግስት በአሸባሪው የህወኃት ቡድን ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ድርጅታቸው ቀድሞ ምላሽ መስጠቱን አውስተው የሚጠበቅባቸው ሁሉ ለማድረግ ድርጅታቸው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሲሳይ ነጋሽ ከእኩልነትና ነጻነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በውጭ ለሚገኙ ጽንፈኛ ዲያስፖራዎች ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት በማቆም ሚዛናዊነታችሁን ልታሳዩ ይገባል ብለዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ አሸባሪው የህወኃት ቡድን ከመደገፍ ተቆጥበው ከመንግስት ጎን ተሰልፈው አጋርነታቸው ሊያሳዩ ይገባል፤የውጭ ሃይሎችም ይህን የሽብር ቡድን በተለያዬ መንገድ ድጋፍ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ማቆም አለባቸው ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አገርም እየደረሰ ያለውን ጫና እንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይታቸውን የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡