ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ
ለአሻጥረኞች እኩይ ሴራ መሳሪያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስትና ህዝብ ሀገራችን ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ከገጠማት ፈተና ለመታደግ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ርብርብ በማድረግ ላይ ነው፡፡
በአንድነት ከቆምንና ተደምረን ከተጋን ይኽን ፈተና አሸንፈን፣ ችግሩን ወደ ዕድል፣ ዕድሉንም ወደ ታላቅ ድል ለውጠን፣ ሀገራችንን ወደ የሰላምና የብልጽግና ከፍታ ማማ ላይ እንደምናደርሳት ለአፍታም አንጠራጠርም፤
ኢትዮጵያ ሀገራችን ሁሌም ምጥና ጣር ቢበዛባትም እንደብረት እየጠነከረች በፈጣሪዋና በህዝቦቿ ጥረት ከሚገጥሟት ፈተናዎች በማይታመን ሁኔታ ትንሳዔዋ እየደመቀ የምትሄድ ሃገር ናት፡፡ ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሟትም ፈተናዎችና ያለፈችባቸው መንገዶች ይህን ሀሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው::
የክልላችን ህዝብ የሀገሩን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ከዳር እስከ ዳር በተንቀሳቀሰበት በዚህ ወሳኝ ወቅት አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ከኢትዮጵያና ከህዝቦቿ በተጻራሪ በመቆም የያዙትን የጥፋት ተልእኮ በግልጽ መናዘዝ ጀምረዋል::
እነዚህ ሁለት ያበቃላቸው የሽብር ኃይሎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ቢዶልቱም ኢትዮጵያን የሚነቀንቅ ድፍረትም፤ጉልበትም ሊኖራቸው አይችልም::
ለዚህም ነው የክልላችን ህዝብ ”ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም በምንም” በሚል መሪ ቃል እየተመራ የህልውና ዘመቻ ላይ የሚገኘው።
ይህን ቁርጠኝነቱን ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብና በመልበስ ጭምር በየከተሞቹ ባካሄዷቸው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ስብሰባዎች እያረጋገጠ ነው።
የህዝቡ የደጀንነት ማረጋገጫ ቃል በመግባት ብቻ የተገታ አይደለም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መከላከያን እየተቀላቀሉ ቃልን በተግባር ማሳየት ጀምረዋል።
የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ህዝቡ መከላከያን በገንዘብም በአይነትም እየደገፈ ነው። እናቶች ልጆቻቸውን ስመው ወደ ግንባር ሸኝተዋል።
በዚህ ብቻ ሳያበቁ ፤ የሚችሉትን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጓዳኝ ወገባቸውን አስረው ለሠራዊቱ የሚውል ስንቅ እያዘጋጁ ናቸው።
ባለሀብቶች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመተባበር ሰንጋዎችን፣ በጎችን፣ ፍየሎችንና ገንዘብን ሠራተኞችም የወር ደመወዛቸውን እየሰጡ ናቸው።
ይህ የህዝቡ አጋርነት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ትልቅ ስንቅና ደጀን ነው።
ይሁን እንጂ ሕዝባችን ለዘመናት ከተጣበቀው ድህነትና ከዚህ ከሚመነጨው ጉስቁልና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ለመሻገር በተነቃቃ ማንነትና እልህ ውስጥ ቢገኝም ለግል ጥቅም ሲሉ ሀገራቸውን ክደው ከጥፋት ሀይል ጎን የሚያሰልፋቸውን ተግባር የሚሸርቡና የሚጎነጉኑ ብለውም የሚሳተፉ ጥቂት የሚባሉ የእናት ጡት ነካሾች አልታጡም፡፡
ይህ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብና ከዚህ የሚመነጨው ክፋት የሚፈጥረው ሰብአዊ ቀውስ እና ሀገር ማፍረስ የቱን ያህል ንጹሀንን ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ ለመረዳት ከሞቀ ቀዬአቸው ወጥተው በጊዜያዊ መጠለያ ላይ ያሉ ዜጎችን መመልከት በቂ ነው።
በሀገር ጠላትነት ከውስጥም የተሰለፈ ይሁን ከውጭ ዓላማው ህዝብን ማጥፋት ማውደም እና ማዋረድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ በዝምታ የሚታይ አይሆንም፡፡
ይህ የህዝቡ ትብብርና ጀግንነት ያስደነገጣቸው የውስጥና የውጪ የጥፋት ሀይሎች ባወጁት ይፋዊ ጦርነትና በጀመሩት የሽብር ተግባር መዝለቅ ሲያቅታቸው እና ማጣፊያው ሲያጥራቸው እንደ አበደ ውሻ ሁሉንም መልከፍና መንከስ ቀጥለውበታል፡፡
ተባባሪዎቻቸው የሆኑ የወቅቱ ሁኔታ መልካም አጋጣሚ የፈጠረላቸው መስሏቸው የማይገባቸውን ሀብት ለማካበት እና በህዝብ ላይ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ የሚሯሯጡ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳሉ እየታዩ ነው፡፡
እነኚህ ራስ ወዳድና ለህዝብና ለሀገር ወገናዊነት የሌላቸው ግለሰቦች በኢትዮጲያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተው ከአሸባሪው የሕወሐት ጁንታ የሚለዩ አይደሉም፡፡
ስለዚህ ያለ ዕውቀት ሀብት ለማካበት ብቻ በዚህ የሀገርና ህዝብ ክህደት ተግባር ውስጥ የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች ለአሻጥረኞች እኩይ ሴራ መሳሪያ እንዳትሆኑ እጃችሁን በፍጥነት እንድትሰበስቡ መንግስት ያሳስባል፡፡
በአመለካከትና በድርጊት የባንዳነትና የተላላኪነት ተግባር ለመወጣት የንግዱን ስርዓት ለማዛባት በህዝብ ላይ ኑሮውን ለማክበድ በዘመታችሁ ቡድኖች ላይ ግን መንግስት አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ያስታውቃል፡፡
ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ግን ሕዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን ህገወጥ የምርት ክምችት እና የግብይት ሥርዓቱን ለማዛባት የሚደረገውን አሻጥር በማጋለጥ እንዲተ ባበር ጥሪ እናደርጋለን፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከህዝብ እና ከመንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት ችላ በማለት የህዝቡን መብትና ጥቅም በሚጎዳ ሀገርን በሚያፈርስ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ በተገኘ የመንግስት የስራ ኃላፊም ሆነ ባለሙያ ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ኢትዮጲያን ለማዳን እዘምታለሁ፤የትም፤መችም፤ በምንም!
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት
ነሐሴ 11/2013