የሰላም ጓድ አባላት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሰት ጎን እንደሚቆሙ ገለጹ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከተመራው የሰላም ጓድ አባላት ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
የሰላም ጓድ አባላት በአገራችን እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች በመደሰታቸው ምስጋና ለማቅረብ እና አሁን በአገራችን ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሰትና ህዝብ ጎን መቆማቸውን ለማረጋገጥ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የቡድኑ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካን አገር ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የቡድኑ አባላት በማሳተፍ በልማት ሥራዎች ፣በተራድኦ ተግባራት እና በአገር ገጽታ ግንባታ እያበረከቱ ያሉት የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ለአቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ደመቀ ቡድኑ እያደረገ ስላለው በጎ ተግባራት እና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆማቸው ምስጋና አቅርበው፤ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ በተያያዘም መንግስት የቡድኑን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው አረጋግጠዋል ሲል የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።