በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ችግር ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው ሽብርተኛው የህወሓት አመራር ብቻ ነው – ዶክተር አረጋዊ በርሄ
በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ሰብዓዊ ችግር ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው ሽብርተኛው የህወሓት አመራር ብቻ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበርና የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ አስታወቁ።
ዶክተር አረጋዊ እንዳስታወቁት፥ ጁንታው ቡድን እንኳን አሁን ህዝቡ በዚህን ያህል ስቃይ ውስጥ ገብቶ ይቅርና ለውጡን አልቀበልም ብሎ ከኮበለለበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰቱ ለነበሩ ቀውሶችም ሆነ አሁን እየተፈጠረ ላለው እልቂት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው እርሱ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ሽብርተኛው የጁንታው ቡድን የህዝቡ መቸገር መራብ ምንም ጉዳዩ ባለመሆኑ እርዳታ የጫኑ 169 ከባድ መኪኖች አፋር ክልል ላይ እንዳይንቀሳቀሱ ጥቃት መክፈቱን ገልጸዋል፡፡
ይህ ተግባሩ የሚያሳየው ቡድኑ ለህዝቡም ለሃገርም ጠንቅ መሆኑንና የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ ነው ብለዋል።
ህዝቡ በጦርነትም ይሁን በረሃብ እየተሰቃየ ባለበት በዚህን ጊዜ የእርዳታ መግቢያ መስመርን መዝጋት ወይም ጥቃት ለመፈጸም መነሳት ከፍተኛ የሆነ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት ከመሆኑም በላይ አካባቢውን ሁሉ በሱ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ እንዲታመስ ሆን ብሎ ያቀደውና የፈለገው ነገር ነው ብለዋል ዶክተር አረጋዊ፡፡
ይህ ደግሞ ህዝቡም ሊገነዘበው ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ሁሉ ሊያዩትና መፍትሔ ሊሰጡት የሚገባ እኩይ ተግባር መሆኑን መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።