ዴሞክራሲ እና ሃገር አሸንፈዋል
ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ሽግግር ላይ የምትገኝ ሃገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር ተፈተዋል፤ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ሀይሎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ እና በሰላማዊ ትግሉ እንዲቀላቀሉ እድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ከለውጡ በፊት ማነቆ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ህግ፤ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ ጨምሮ ሌሎች ህጎች እንዲሻሻሉ ተደርገዋል፡፡ እንደ ምርጫ ቦርድ፤ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትም ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁ መደረጉ ሃገሪቷ የዴሞክራሲ ሽግግር ላይ ስለመሆኗ በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ምርጫ በአንድ ሀገር ላይ የዘመናዊነት መገለጫ እንደሆነ ይታወቃል:: በተለይ በሀሳብ የበላይነት ዜጎች ይበልጥ ተጠቃሚ የመሆን ተስፋቸው የሰፋ ይሆናል:: ምርጫ የሃገርና የራሳችንን የወደፊት እድል የምናረጋግጥበት ቁልፍ መሳርያ ነው:: አመዛዛኝና ልባም ዜጎች የሚፈልጉትን መሪ ለመምረጥ እንደ አይነተኛ መንገድ ይጠቀሙበታል ምርጫን፡፡
በ2012 ዓ.ም. ሳይካሄድ የቀረው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በተለይ በኮሮና በሽታ ሳቢያ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዳይካሄድ አድርጓል፡፡ በሂደት ስጋቱ እየቀነሰ መምጣቱ ሲታወቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው ዘንድሮ /2013/ እንዲደረግ በወሰነው መሰረት ታሪካዊው 6ኛው ሃገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሃገር እና ህዝብ አሸናፊ በማድረግ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ለየት የሚያደርጉት በርካታ አዲስ ክስተቶች እንደነበሩ ማየት ይቻላል፡፡ ምርጫውን የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ከጅምሩ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ መደረጉ ትልቁና ወሳኙ ምእራፍ ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ዘንድሮ የተካሄደው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ የዜጎችን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከማንኛውም አካል ነፃ በሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም እንዲመራ ሆኗል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን አመላመልና አሿሿም ግልጽ በሆነ ሁኔታ መከናወኑ ሌላው በተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በመራጩ ህዝብ ዘንድ እስካሁን ከተደረጉት 5 ምርጫዎች የተሻለ ተአማኒነት እንዲኖረው አድርጎታል፡፡
የምርጫ ቦርድ አዲስ አደረጃጃትን ተከትሎ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ይሄም ምርጫው ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
የዘንድሮ 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ከ37 ሚልዮን በላይ ሰዎች በምርጫው መሳተፋቸው ዜጎች በቀጥታና በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸውን በተግባር ላይ ለማዋል ከፍተኛ መነሳሳት የታየበት ሂደት ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥ ሲቪክ ማህበራትና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን በሚገባ የመታዘባቸው እውነት ለዘንድሮው ሃገራዊ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ በር ከፍቷል ማለት ይቻላል፡፡
የቅድመ ምርጫው ሂደት አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቅድመ ምርጫ አንድ ምርጫ ተአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆኑን ከምናውቅበት ሂደትና ማሳያ አንዱ ነው፡፡
በቅድመ ምርጫው ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት ያደረጉበት እንዲሁም ምዝገባ ያከናወኑበት ነበር፡፡ የህግ ማእቀፍ ዝግጅትም ተደርጓል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠና እና ምደባ፣ የምርጫ ክልልን የማካለል ሥራዎች፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የፆታ አሳታፊነት፣ ሁሉ በዚህ ቅድመ ምርጫ ሂደት በሚገባ የተከናወነበት ወቅት ነበር፡፡ የብዙሃን ማኅበራት አሳታፊነት፣ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ፣ የብዙሃን መገናኛዎች የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋት እና በጥልቀት የተከናወነበት እንደነበር በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ወቅት በምርጫ አስፈጻሚው ተቋም እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መጠነ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ ነበር ለማለት በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ከመሆኑ ባሻገር እንደ አገር አሸናፊ የሆንበት ነው ለማለት ያስቻለን ዋናው ጉዳይ የምርጫ ወቅት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ነው፡፡ በምርጫ ወቅት የነበሩ ሂደቶችን ስንመለከት በርካታ ወሳኝ ተግባራት የተከናወኑበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራው፤ የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት አገላለጽ እና መሰል ሂደቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፤ ታዛቢዎች በተካተቱበት መልኩ መሆኑ እንደ ማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡
መራጩ ህዝብ ከጧት አንስቶ በተረጋጋ እና ከተፅእኖ ነፃ በሆነ መልኩ እስከ ማታ ዝናብና ብርድ ሳይበግረው በምርጫው መሳተፉ እወነትም የምርጫውን ሰላማዊነትና ዴሞክርሲያዊነት ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡
በአጠቃላይ በቅድመ ምርጫ ሂደቱ እና በምርጫ ወቅት የነበረው ሂደት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ እስካሁን ከነበሩት ምርጫዎች በእጅጉ የተሻለ እንደ ሃገር የዴሞክራሲ መሰረት የተጣለበት፤ ወሳኝ እና ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ተስፋ ያላት ሃገር ስለመሆኗ ያመላከተበት ክስተት ነበር ማለት እንችላለን፡፡
ለዚህ ምርጫ ስኬታማነት የዴሞክራሲ ተቋማትና ህዝቡ ከጅምሩ አንስቶ የድርሻቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ የምርጫ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ ብዥታዎችን በማጥራት ዴሞክረሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ሚና መጫወታቸው ሌላው በምርጫው ሃገር እና ዴሞክራሲ እንዲያሸንፉ የነበረው አስተዋፅኦ ትልቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ፖሊሲና ስትራቴጅ በግልጽ ለህዝቡ እንዲደርስ በማድረግ እና አላስፈላጊ ብዥታዎች በምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፉ በማስቻል ረገድ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ተወጥቷል፡፡
የሲቪክ ማህበራት ለማህበረሰቡ የምርጫ ትምህርት እና መብቶችን በማሳወቅ ረገድ የነበራቸውም ንቁ ተሳትፎም የዘንድሮውን ምርጫ እንዲሳካ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡
በርከት ያሉ ደጋፊዎች ያሏቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተደረገው ምርጫ ሰለማዊነት የነበራቸው ሚናም ቀላል አልነበረም፡፡ ነጻ፣ ተዓማኒ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ገዢዉ ፓርቲ የነበረበትን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣቱም በምርጫው ከምንም በላይ ሃገር እና ህዝብ አሸናፊነት እንዲኖረው አስችሎታል፡፡
ምርጫው አንዱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል እንጂ የሁሉም ነገር መወሰኛ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ሀገሩን አክብሮ ከማለዳ እስከ ምሽት ድምጹን መስጠቱ፤ ፓርቲዎችም የተሰጠውን የድምጽ ውጤትም በማክበር ለሀገርና ለሕዝብ ያላቸውን አክብሮት በተግባር የሚያሳዩበት ወቅት መሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆኑበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡