ለወዳጆቻችንና ለባለ አገሩ ደስታንና ተስፋን፤ ለሩቅና ቅርብ ጠላቶቻችን ደግሞ ብስጭት ጥሎ ያለፈ ሁነት… / በአብዲ ኬ/

ለወዳጆቻችንና ለባለ አገሩ ደስታንና ተስፋን፤ ለሩቅና ቅርብ ጠላቶቻችን ደግሞ ብስጭት ጥሎ ያለፈ ሁነት… / በአብዲ ኬ/

  • Post comments:0 Comments
ባሳለፍነው ሰኞ ማለትም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ በብዙ መመዘኛ የተሳካ ምርጫ አካሂዳለች፡፡ ይህ ደግሞ ለወዳጆቿና ለምርጫው ባለቤት ህዝብ ደስታን፤ ለሩቅና ለቅርብ ጠላቶቿ ደግሞ መደናገጥንና ብስጭትን ፈጥሯል፡፡
ምርጫውን አስታኮ አገሪቱን ለማመስ የቋመጠው ኃይል ህልሙ ቅዠት ሆኖበት አልፏል፡፡ የእነዚህ ኢትዮጵያን ካለችበት ከፍታ ለማሳነስ የሚራወጡ ኃይሎች እኩይ እቅዳቸው ገና ከጅምሩ የከሸፈባቸው ይምስላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለአገሩ ጉዳይ እንኳን ካርድ ይዞ እጣፋንታውን መወሰን ይቅርና ደረቱን ለጥይት ሰጥቶም ለአገሩ ለመሞት ዝግጁ የሆነው ህዝባችን አድዋ ላይ አባቶቻችን እንደጻፈት ታሪክ ዳግም አዲስ ታሪክ ጽፏል፡፡
ሁላችንም እንደተመለከትነው አለም ሁሉ፤ በአግራሞት ሲታዘብ እንደነበረው ህዝብ ድምጹን ለሚፈልገው ፓርቲና ግለሰብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመሰጠት ሃላፊነቱን ለመወጣት ያሳየው ቁርጠኝነት ልዩ ነበር፡፡ በለሊት ወጥቶ ሲሰለፍ ብርድና ጤዛ አልበገረውም ነበር፤ ሙሉ ቀን ወረፋ ይዞ ተሰልፎ ረዥም ሰዓታት ሲቆም ፀሃዩ ምንም አለመሰለውም ነበር፤ አገሩን ለማሻገር አድዋ ላይ እንደተሰለፈው ጦርና ጋሻ እኩል ዋጋ ያላትን ካርዱን ለሚፈልገው ፓርቲና ግለሰብ ለመስጠት ዝናብና ብርድ አላገዱትም ነበር፡፡ ህዝባችን እስከ እኩለ ለሊት ድረስ ወረፋውን ጠብቆ ድምጹን ሰጥቶ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡
እኔም እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ወደምርጫ ጣቢያ ስሄድ ባየኋቸው ረጃጅም ሰልፎች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ለአገራቸው ሟች መሆናቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ በእርግጥም አነዛ ረጃጃም ሰልፎች ለዓለም ትልቅ መልእክት እያስተላልፉ ነበር፡፡ አገር ማለት ይህ ነው፡፡ አገሬው በአገሩ ጉዳይ ወሳኙ ራሱ መሆኑን ከቃለ ባለፈ በተጨባጭ ያሳየበት በሁላችንም አዕምሮ ታትሞ የሚኖር ሁነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእኔ ምልከታ ይህ በአንድ በኩል አገር ወዳድነትና አርቆ ማሰብ ነው፤ ለምን ቢባል ያች ቀን፤ ያች ህዝቡ በእጁ የያዛት ካርድ የሚቀጥሉት 1825 ቀናት የአገሪቱን እጣፋንታ የምትወስን ናትና፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ተረድቶ ሃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት፤ የመሰልጠን ምልክት ነው ተብሎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም፡፡
የአገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል ያገባኛል የተሻለ ነገር ይገባታል ብሎ፤ ፖሊሲ ነድፎ፤ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ ደፋ ቀና ብለው ሲሰሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፤ ያሳዩት አገር ወዳድነትና ሰላማዊነት ለዚህ ምርጫ ስኬት የነበራቸው ሚና በምንም የማይተካ ነበር፡፡
በብዙ ችግርና ያልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ህዝቡ እንዲሳተፍና በአገሪቱ የነገ እጣ ፋንታ ላይ እንዲወስንም ሲያበረታቱ ነበር፤ በምርጫው እለትም ደስ በሚል መልኩ ሂደቱን ሲከታተሉ፤ ከመመረጣቸው በላይ የዴሞክራሲ መተከል፡ የአገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ ባህል መሸጋገር እንደሚያሳስባቸው ለህዝብ ሲገልጹ ነበር፡፡
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የህዝቡን ውሳኔ እንደሚያከብሩም በአደባባይ እየተናገሩ ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የመሸጋገር ተስፋን በህዝቡ ልብ ውስጥ እንዲለመልም ስያደርጉ ነበር፡፡ ይህ የሚደነቅና የሚመሰገን ነገር ነው፡፡
ይህም ለአገር ወዳዱ ህዝብ ደስታ ሲፈጥር እነሱን ተጠቅሞ ህዝቡን እየማገዱ አገሪቱን የግጭትና ያለመረጋጋት አዙሪቱ ውስጥ ለመክተት ለሚራወጥ ኃይል መርዶ ነበር፡፡ መንግስትም ሃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣቱ ምርጫው ያለ አንዳች የጸጥታ ስጋት ተካሂዷል፡፡ ለዚህም የጸጥታ ሃይላችን ሊመሰገን ይገበዋል፡፡
የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው እንግዲህ አገርና ህዝቧን ያኮረ፤ ጠላቶቿን ያሰፈረ የምርጫ ሂደት ነው የሆነው፡፡
አሁንም ክብር ለአገሬ ኢትዮጵያ!

Leave a Reply