ብልጽግና ማንኛውም ነገር ከኢትዮጵያ በላይ ሊሆን አይችልም ብሎ ያምናል፡፡ብልጽግና ከአገር በታች እንጂ በላይ አድርጎ አይቶ አያውቅም፤ሊሆንም አይችልም፡፡የብልጽግና ህልውና ከአገር ህልውና ጋር እንዲሰፋ አይፈልግም፡፡ብልጽግና ከስልጣን ቢወርድ ወይም ቢፈርስ የምትቀጥል ጠንካራ አገር ነው የሚፈልገው፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጽግና የኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ነው፤አልተቀየራችሁም ሲሉን ይደመጣሉ፡፡በእርግጥ ለውጥ ለማምጣት የተሄደበት መንገድ ከዚህ ቀደም ያልተሞከረ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ሁልጊዜ ለውጥ የሚመጣው በአብዮት መልክ ነው፡፡ሰዎች ይገደላሉ፤የካቢኒ አባላት አንድ አዳራሽ ላይ ይገደሉ ነበር፤የነበረው ሁሉ ይፈርስ ነበር ከዛ እንደ አዲስ ይጀመራል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እና ስልጣን ደረጃ የሚቀመጡ አገሮች በዚህ ዓለም ሶስትና አራት ናቸው፡፡በተቋማት ግንባታ በድህነት ደረጃ ግን የዛሬ አምስት ዓመት የተቋቋምን አገር ነው የምንመስለው፡፡የወረስነው ትልልቅ ተቋሞች እንዳልነበሩ ሁሉ ላሊበላን፣አክሱምን፣ፋሲለደስን፣ሐረር ጀጎልን የሰሩ የታላላቅ ህዝቦች አገር እንዳልነበርን አፍርሰን እየሰራን ከዜሮ እየጀመርን መልካሙን እያስቀጠልን መጥፎን ደግሞ እየቆረጥን መጣል ባለመቻላችን መልካሙንም ሆነ መጥፎውን የሚያፈርስ የፖለቲካ ባህል ስላለን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ከዜሮ እየጀመረች እንድትቀጥል አይፈልግም፡፡የአብዮት መንገድ አላዋጣንም፤ሁሌ ጀማሪ አድርጎናል፤የፊት ቀዳሚዎች ሆነን ወደ ኋላ አድርጎናል፡፡የዛሬ ሶስት መቶና አራት መቶ ዓመት የተመሰረቱ አገሮች ስንዴ እየረዱን ነው፤በሺህ ዓመታት የሚቆጠር ታሪክ ያለን አገር ሆነን እያለ፡፡ስለዚህ ኢህአዴግ ውስጥ መጥፎም ጥሩም ነገር አለ፡፡ጥሩውን ነገር አስቀጥላለሁ፤መጥፎውን ነገር ቆርጬ እጥላለሁ ያለ ፓርቲ ነው ብልጽግና፡፡
ብልጽግና ፓርቲን ይምረጡ