የአድዋ ድል ኢትዮጵያዉያን ወራሪ ጠላትን ድል ያደረጉበት ብቻ አይደለም፤አድዋ ኢትዮጵያዉያን በአንድነትን ትብብርን ያሳዩበትም ጭምር ነዉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አባት እና እናቶች ለዚህ ትዉልድ ያቆዩት ጠንካራ የማስተባበር፤ የመምራት፤ የመደማመጥ ችሎታቸዉም እንዳላቸዉ ያስመሰከሩበት ድል ነዉ።አድዋ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያንና በሌሎች አህጉሮችም በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች የተስፋ ጭላንጭል ያሳየ ድል መሆኑን ዓለም ይረዳዋል፡፡
የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ብቸኛ ነፃ የጥቁር ሃገር ሆና እንድትቆይ አባቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ መላዉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ እጅግ የሚኮራበት ድል ነዉ። ምክንያቱም አድዋ ታሪክን ቀይሯል። የአድዋ ድል አሜሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁር ዜጎች እንደ ትልቅ የነጻነት ምልክት ሆኖ ይታያል። አንድ ጥቁር ንጉስ ሕዝቡን አስተባብሮ በዓለም ላይ በታላቅ ስም በታላቅ ክብር ሃገሩን ነጻ አድርጎ መኖር የሚችልበት አዲስ ታሪክ የተፃፈበት ብሔራዊ ክብራችን ነው፡፡