የዓድዋ ድል ጽናትን የብልጽግና ጉዞአችንን እውን ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል!

የዓድዋ ድል ጽናትን የብልጽግና ጉዞአችንን እውን ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል!

  • Post comments:0 Comments

በዜማ ያሬድ

የካቲት ወር በአፍሪካውያን የታሪክ ሂደት ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ለመላው ጥቁር ህዝቦች! ለአፍሪካውያን የድል ወር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አፍሪካውያን በግፍ የሚረገጡበት፣ እንደ ሸቀጥ የሚሸጡበትና በባርነት የሚገዙበት፤ ለአፍሪካውያን የጨለማና ክፉ ዘመን ነበር ያ ዘመን፡፡

አፍሪካውያን በአገራቸው በጉልበታቸው አምርተው፤ የአገራቸው ምድር የሰጠቻቸውን ገፀ በረከት በነፃነት መጠቀም ሲገባቸው ባይተዋር ሆነው እየተገረፉና እየተናቁ በነጮች ባርነት ሲገዙ የነበረበት ክፉ ዘመንም ነበር የቅኝ ግዛቱ ዘመን፡፡

በርካታ አፍሪካውያን በነጮች ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው መራራውን ጊዜ በሚገፉበት በዚያን ዘመን እምቢ ለባርነት! እምቢኝ! ለግዞት ያሉት ጀግኖች አባቶቻችን የቅኝ ገዢዎችን ቅስም በመስበር አገራችን በጠላት ወረራ የማትደፈር ክብርት ሀገር መሆኗን አስረግጠው መልዕክት ያስተላለፉበት፣ ለአፍሪካውያንም ኩራት የሆኑበትን ድል የተጎናፀፉበት ወር ነው ወርሃ የካቲት፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከጣሊያን ጋር በተካሄደው ጦርነት የአገራችን ጀግኖች አባቶቻችን እንደዛሬው ዘመናዊ ትጥቅ ሳይኖር፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያም ሳይሸከሙ በባዶ እግራቸው አድዋ ዘምተው አስፈሪውን የጣሊያንን ጦር ድል በማድረግ የማይገፋውን ገፍተው ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነ ድል ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

የአድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበረ፤ ጣሊያንን የሽንፈት ካባ ያከናነበ፤ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት በምድር አውሮፓም እንደተአምር እንዲወራ የኢትዮጵያ ስምም ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያስቻለ ድል ሆነ፡፡ ይህ ድል ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እስከ 1960ዎቹ በቅኝ ግዛት ሲማቀቁ፤ ሲበዘበዙ፤ ሲጨቆኑ እኛ ግን ከባርነት ቀንበር ነፃ በመውጣት ሰላማዊ አየር እንድንተነፍስ አስችሎናል፡፡ ይህች ታፍራና ተከብራ የኖረችው አገራችንም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በማቋቋም ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ለሌሎች ነጻ መውጣት ጭምር የላቀ አስተዋፅኦም አበርክታለች፡፡

የካቲት ወር የአድዋ ወር በሚል ተሰይሞ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ ይህ ወር የዓድዋ ወር ሆኖ መሰየሙ አዲሱ ትውልድ ድል ከመዘከር ባሻገር አባቶቹ ያስረከቡትን የታፈረችና የተከበረች አገር ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት አላቆ አዲስ ድል እና አዲስ አሻራ እንዲያሳርፍ እድልም፤ ማበረታቻም የሚሆን ነው፡፡

የዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችን የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬ ትውልድ ደግሞ በመለወጥ ላይ ያለችውን አገራችንን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ በማደረስ አዲስ ታሪክ መፃፍ ይገባዋል፡፡ በወንድማማችነት እና በመተባበር መንፈስ ውስጥ ሆነን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ድል ለማድረግ መትጋት ይገባናል፡፡

የአገራችንን ብልጽግና እስክናረጋግጥ ድረስ የጀመርነው የለውጥ ዘመቻ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገራችን ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ አገራችንን የተሻለች አገር አድርጎ ማስቀጠል የዚህ ትውልድ አደራና ታሪካዊ ግዴታ ነው፡፡

በዓድዋ አባቶቻችን የጠላት ወራሪን ለመመከት የከፈሉትን ዋጋ ዛሬ ድህነትን በማስወገድና አገራችንን ካደጉት አገራት ተርታ በማሰለፍና ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን በማረጋገጥ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ለመሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረብ ይኖርብናል፡፡ ሰላም፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና መስዋዕትነት ለዘለዓለም ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!!

Leave a Reply