ግብጾች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የያዙትና እያራምዱት ያለው የፖሊሲ ሐሳብ የትም እንደማያደርሳቸው ኢትዮጵያዊያን ሆነ ግብጻዊያን በአግባቡ ይረዱታል፡፡
ግብጽ ለዘመናት በከንቱ እያሰማችው ያለው የቁራ ጩኸት ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማሳጣት ቢሆንም በኢትዮጵያ መንግስት ተንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እንዳሰበችው ሳይሆን እዚህ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ይህ ማለት ግን የዓባይ ፖለቲካ በቀጣይ ፈተናዎች አይገጥሙትም ማለት አይደለም፤ከባድና እልህ አስጨራሽ እንቅፋቶች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡
ግብጽ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም መንገራገጭ እንደ ትልቅ ዕድል በመጠቀም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል የማትፈነቅለው ድንጋይ፣ የማትደርስበት ደጅ የላትም፡፡ሲሻት የአረብ ሊግ ሀገራትን እንደማስፈራሪያ ትጠቀምባቸዋለች፤ሌላ ጊዜ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በዋናነት ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን በመጠቀም በግድቡ ግንባታ ላይ ጫና ለመፍጠር ትሞክራለች፡፡
የዓባይ ፖለቲካ ዛሬም ድረስ በቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ተሸብቦ በአዲሱ የቅኝ ግዛት እሳቤ የተሸበቡት ፈርዖኖች ዛሬም በ1929 እና 1959 ስምምነት የመሟገቻ እና የአሳሳች ዲፕሎማሲያቸው መጋመጃ አድርገው እየባዘኑ ነው።
የግብፆች ግብ እንደ ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት መንፈስ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት መመዝበር ነው።ዓባይ ለኢትዮጵያ ወንዝ ብቻ አይደለም ባሃል፣ሃይማኖት ፣ቅኔ እና አፈር ነው።ካይሮዎች ይህን በበላይነት ያለ ማንም ከልካይነት መዝረፍ ይፈልጋሉ በእርግጥ ሲዘርፉም ከርመዋል።
ጋዜጠኛ ስላባት ማናዬ የዓባይ ፖለቲካ በሚለው መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ሲል ያስነብባል፡፡ዓባይ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ታሪኩ፣ጥበቡ፣ትውፊቱ፣ሁለንተናዊ ኑባሬው እንዲሁም የዕሴቱ መገለጫ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ጋዜጠኛው ቀጥሎም ዓባይ ለኢትዮጵያዊያን መቀነት ነው፤ጣናን ሐይቅ እንደ ዕንቁ ፈርጥ ቢወከል በፈርጧ ውስጥ ተሰክቶ የሚያልፍ የኢትዮጵያን አንገት ያስዋበ ጥቁር ማተብ ነው ሲል ጠንከር አድርጎ ገልጾታል፡፡
እርግጥ ነው ዓባይ ለኢትዮጵያዊያን ያለውን ትርጉም ከዚህ በላይ ሊገለጽ ይችላል፡፡ዓባይ ለኛ ኢትዮጵያዊያን ሁለመናችን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ሲርበን አሳ አጥምደን የምንበላበት፣የግል ንጽህናችንን ለመጠበቅ ልብሳችንንም ሰውነታችንንም የምናጥብበት፣ሲጠማን አንጀታችንን ለማራስ የምንጎነጨው ወንዛችን ነው ዓባይ፡፡
ዓባይ መነሻውን ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ ቢሆንም በአግባቡ ተጠቅመን ህዝባችንን ከድህነት አረንቋ ማውጣት አልቻንም፡፡የኢትዮጵያን ንጹህ ውሃ እየጠጣጭ፣ወንዙን ተጠቅማ ከምታገኘው ልማት እየበላች ጥጋብ አላስተኛት ያለችው ሀገረ ግብፅ የኢትዮጵያ መንግስት ህዝብ ዓባይን በመገደብ ለመጠቀም ያሳዬው ተነሳሽነት ምቾት ነስቷት ሕልውናዬ ይናጋብኛል፣ዘጠና አምስት በመቶ ህዝቤ ወንዙን ተከትሎ የሚኖር ስለሆነ ለከፍተኛ ረሐብ ይጋለጥብኛል በማለት ጩኸቷን ማሰማት ጀመረች፡፡
ያም ሆነ ይህ ግብጽ በአባይ ዙሪያ ያላት የተሳሳተ አመለካከት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከመጨረስ አያግዳትም፡፡ኢትዮጵያዊያን ግድባችንን ጨርሰን በጨለማ ከመኖር ወደ ብርሃናማው ህይወትና ወደ ብልጽግና ልንሸጋገር ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርተውናል ፡፡ግድባችንን አጠናቀን በድቅድቅ ጨለማ የሚኖረውን ህዝባችንን የብርሃን ካባ አልብሰን የድህነት ታሪካችንን ለመቀየር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡
በመጨረሻም ተወዳጇ ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው ሁለንተናን በሚወሰውስ ዜማዋ ዓባይን ከፍጥረቱ እስከ ፍሰቱ ዓባይ ወንዛ ወንዙ ስትል እንዲህ ስትል አንጎራጉራለች፡፡
የማያረጅ ውበት፤የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ፤ለዘመናት የጸና
ከጥንት ከጽንሰ አዳም፤ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት
ግርማ ሞገስ፤የአገር ጸጋ የአገር ልብስ፤
ዓባይ ዓባይ የበረሃው ሲሳይ…
ዓባይ የወንዝ ውሃ፤አትሆን እንደሰው
ተራብን ተጠማን ተቸገርን ብለው
አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን ያስቀምጠሃል በግብጾች ከተማ
ዓባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው መዘዙ… ትለዋለች፡፡
በህብር ወደ ብልጽግና !