ቅድመ ምርጫና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀላፊነት /በሚራክል እውነቱ/

ቅድመ ምርጫና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀላፊነት /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያስተሳሰረው የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር ገመድ እንዳይበጠስ ምን መደረግ አለበት? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የሁሉም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ከሚጠቀሱለት የጋራ እሴቶች መካከል ዋነኛው ለአገሩ ያለው ጥልቅ ፍቅር ነው፡፡ይህ የእኛ ኢትዮጵያዊያን መለያችን ነው፡፡ ይህ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ የዘመናት እሴት ሆኖ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፤ምንም እንኳ ትልቁን ሀገራዊ ምስል ለማደብዘዝ የሚጥሩ ሀይሎች ቢኖሩም፡፡

ኢትዮጵያ የምትባለው የጀግኖችና የጨዋ ኢትዮጵያውያን አገር ለዘመናት የውጭ ወራሪዎችና የሀገር ውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች ቢፈትኗትም ከቶም ሊሳካላቸው ግን አልተቻላቸውም፡፡ ይህች ታሪካዊ የጀግኖች አገር ህልውናዋ አስተማማኝ ሆኖ መቀጠል ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው ማንኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ወይም ጥቅም ከአገር በላይ ሊሆን አይችልም የምንለው፡፡

አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበው የአገሩ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡የሀገር ሉዓላዊነት ተከብሮ ከውጭ ወራሪ ሀይሎች ነፃ የሆነች የተከበረች ሀገርን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡ የህዝብ ፍላጎት ይህ ነው፤ ይህንን ሕዝብ ማክበር ደግሞ የግድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

እያንዳንዱን ጉዳይ ፖለቲካዊ ገጽታ በማላበስ ከተወሰኑ ቡድኖች ዕይታ አንፃር ብቻ ማንገዋለል ለአገርም ሆነ ለህዝብ አይበጅም፡፡ ግለሰቦች ያልፋሉ፣ አገር ግን አታልፍም፤ ይህ ሐቅ ነው፡፡ ይልቁንም የትውልድና የታሪክ ተጠያቂ ላለመሆን ጥረት ማድረግ ይበጃል እንጂ ለህዝብ ፍላጎት መልስ መስጠት የማይችሉ ጉዳዮችን በማንጸባረቅና የግል ጥቅምን መሰረት ያደረጉ አካሄዶችን በመፈለግ መንግስት ሰራ ማስፈታት ለራስም ሆነ ለሀገር አይበጅም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ስለሌለ ነውና፡፡

በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ የፖለቲካ ኃይሎችም ለሕዝብ ፍላጎት ራሳቸውን ማስገዛት አለባቸው፡፡ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰማሩትንም ቢሆኑ ይህ ኃላፊነት ይመለከታቸዋል፡፡ አገር የምታድገውና የምትበለፅገው ሰላም ሲኖራት ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ንፁኃን ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ አገርም ትተራመሳለች፡፡

በተለይ ሀገራዊ ምርጫዎች ሲመጡ ያን ያህል የማይታወቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ የሌለ ሀይላቸውን ተጠቅመው ብቅ ይላሉ፡፡ይህ ሁሌም የተለመደ ግን የማይጠቅም አካሄድ ነው፡፡ለህዝብ የሚታገል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መታገል ያለበት ምርጫን ጠብቆ ሳይሆን በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ከተሰጠው ጊዜ አንስቶ ነው መሆን ያለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ከእንዲህ አይነቱ የይስሙላ አካሄድ መውጣት መሰልጠን ብቻ ሳይሆን ለህዝብና ለሀገርም ተቆርቋሪነትን ያሳያል፡፡

በመከባበር ላይ የተመሠረተ ውይይትና ክርክር ማድረግ ያለ፣የነበረና ወደፊትም ቢሆን ሊሆን የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሚዛን የማይደፉ እና ለህዝብ ቅንጣት ታህል ለውጥ ማምጣት የማይችሉ ክፍተቶችን እየፈለጉ ህዝብንና ሀገርን ለማተራመስ መሯሯጥ የትም አያስኬደንም፡፡ይህንን የተለመደ ጨፍጋጋና ጨለምተኛ መወነጃጀል ማስቀጠል ለማንም አይጠቅምም፡፡ ከዚህ በፊት ያፈራው ፍሬም ሆነ ያመጣው ለውጥ የለምና፡፡

አሁን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሰብ ያለባቸው ጉዳይ ቢኖር መጪው ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ማንም ያሸንፍ ማን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም፣ በአንድነትና በፍቅር ለመኖር የሚያስችለውን አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፍጠሩ ላይ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉ ድርጊቶች ለአገር አይበጁም፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም!

በህብር ወደ ብልጽግና !

Leave a Reply