You are currently viewing

  • Post comments:0 Comments

ከጥቁሩ መጋረጃ ጀርባ የሚታይ የብልጽግና ወጋገን…

በሚራክል እውነቱ

ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ስላሏት የምትፈርስ፣ሰላም የላትም ስለተባለች ዘላለሟን ሰላም የምታጣ ፣አንዳንድ ኑራቸውን በውጭ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ስላሉ ብቻ ከኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና መውረድ ከቶም አይችሉም፤ደሃ ናት ስለተባለች ከድህነት የማትወጣ የሚመስላቸው ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያንጸበርቁ በርካቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ይህ ግን ከንቱ ህልም ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት እምነት ነው፤ለሀገር ውለታ ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉ አባቶች ደምና አጥንት ነው፤ኢትዮጵያዊነት ከራስ አልፎ ስለሌሎች ማሰብ ነው፤ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ኢትዮጵያዊነት ሰብዓዊነት፣ትሁትነት፣ቻይነትና አክባሪነት ነው፡፡ኢትዮጵያዊነት መግባቢያ ቋንቋንችን ነው፡፡

ከጥቁሩ መጋረጃ ጀርባ የሚታይ የብልጽግና ወጋገን አለ፡፡እርግጥ ነው ይህን ወጋገን በቀላሉ መመልከት ላይቻል ይችላል፡፡ዛሬ ዛሬ እያየናቸው ያሉትን ከሰብአዊነት የራቁ ድርጊቶች አደብ ሲገዙ፣ግፈኞች ተለይተው ለፍርድ መቅረብ ሲችሉ፣ኢትዮጵያዊያን በማንነታቸው ኮርተው እንጂ አንገታቸው ደፍተው መኖር ሲያበቁ በጥቅሉ የህግ የበላይነት ፈር ሲይዝ በርግጥም የምንፈልገውን የብልጽግና ወጋገን ያለከልካይ መመልከት እንችላለን፡፡

በየትኛውም ዓለም በለውጥ ጊዜ ችግሮች መፈጠራቸው አንዱ የለውጡ አካል ወይም ባህሪ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡እናት በእርግዝና ወቅት ያንን ፋታ የማይሰጥ ምጥ ችላ ልጅ እንምትወልደው ሁሉ ሀገራችን ላይ የሚገጥሙን ተግዳሮቶች ሁሉ በድል ማሸነፋችን አይቀሬ ነውና ትንሽ መታገስ ጥሩ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን በህብረ ብሔራዊነት የተጋመድን ህዝቦች ነን፡ህብረ ብሔራዊነታችን ኩራታችን፣ አንድታችንና ጥንካሬያችን ከሆነ ይህንኑ መልካም ዕድልና አጋጣሚ ለበጎ ነገር በማዋል ፣ያንተ የእኔ ሳንባባል ተሳስበንና እርስ በእርስ ተከባብረን መኖር ለምን ተሳነን ? ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይንም የህብረ ብሔራዊነት ማሳያ ስለሆነች ብቻ ከድህነት ልናወጣት አንችልም ፡፡

ይልቁንም ከድህነት ጠኔ ወጥተን አንገታችንን በኩራት ቀና አድርገን ለመኖር ከፈለግን ብሎም ሀገራችንን ከልብ የምንወዳት ከሆነ ከልባችን ሌት ተቀን ሰርተን ገፅታዋን ልንቀይርላት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የእያንዳንዳችን አሻራ ያረፈባት የአንድነታችን ውጤት መሆን ስላለባት ማለት ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን በደስታም ይሁን በሀዘን፣በችግርም ይሁን በፌሽታ ለዘመናት አብረን ኑረናል፡፡በተፈጥሮም ይሁን በራሳችን አያያዝ ችግር ምክንያት የሚደርሱብንን ችግሮች እንዴት በብልሀት መወጣት እንዳለብንና  የጠኔውን መድሃኒት በጋራ ሆነን ተማክረን ፣እርስ በእርስ ሀሳብ ተለዋውጠን መፍትሔውን ማግኘት አዲሳችን አይደለም፡፡

ስለሆነም እንደ ሀገር የተጋረጠብንን ፈተና በብስለትና በእርጋታ ተወያይተን ከችግር የመዳኛ መድሀኒቱን በጋራ ሆነን ፈልገን በማግኘት እና የተጋረጠብንን ፈተና በብቃት በማለፍ ህብረ ብሔራዊነታችን የማንነታችን ማሳያ እንደሆነ በተግባር ልናሳይ ይገባናል መልዕክታችን ነው፡፡

ሰላም ለሀገራችን !

ጤና ለህዝባችን !

ምላሽ ይስጡ