በአሮን ተወልደ
አብዛኛው የአገራችን ህዝብ በተቀራራቢ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘ በመሆኑ የሚያነሳቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ተመሳሳይ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከተሞችን ጨምሮ በሁሉም የአገራችን ጫፎች የሚገኙ ህዝቦች ደረጃው ቢለያይም የመሰረተ ልማት፤ የኑሮ ውድነት፤ የግብርና ግብዓት አቅርቦት፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፤ መልካም አስተዳደር፤ ስራ አጥነት እና መሰል ተያያዥ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡
እነዚህን የህብረተሰብ ጥያቄዎች አደራጅቶ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ የህዝብ ይሁንታ ከማትረፍ ባሻገር አምራች ትውልድ ጭምር በመገንባት ቀጣይነት ያለው እድገት ለመገንባት ወሳኝ ነው፡፡
አሁን ባለንበት የእድገት ደረጃ ሁሉንም የህዝብ ፍላጎቶች በአንድ ጊዜ ማሟላት ባይቻልም የሚታዩና ህዝብ የሚቀበላቸው ለውጦች ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡ ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ማጣጣም ያልቻለው ነገር ግን መንግስት በተለያየ ጊዜ ሲገልጠው የቆየው እድገት እንደተወራው እንኳንስ ህዝቡን ሊቀይር ይቅርና ሀገራዊ የእድገት ጮራ ያልደረሰባቸው፤ ድህነትም የጠናባቸው አከባቢዎች አሸን ሆነዋል፡፡
ይህም ‘ልማታዊው’ ልማት ከማምጣት ይልቅ የራሱን የብዝበዛ መዋቅር ከመገንባት የዘለለ ለህዝብ የሚተርፍ ተግባር አለመፈጸሙን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ European Center for Development and Policy Management ባወጣው ጽሁፍ በፈረንጆቹ ሚሊንየም የትግራይ ክልል ከሁሉም ክልሎች በድህነት ቀዳሚውን ስፋራ እንደያዘ ይጠቅሳል፡፡
ከሚሊንየሙ 15 ዓመታት በኋላ ወይም የህወሓት ’ልማታዊ መንግስት’ ስልጣን ከያዘ ከ25 ዓመታት በኋላ እንኳ የትግራይ ክልል ባለበት ከመርገጥ የዘለለ ብዙሃኑን ህዝብ የሚለውጥ ተግባር አልተከናወነም፡፡ ይልቁንም የድህነት ምጣኔ ከጨመረባቸው ሁለት ክልሎች ውስጥ ትግራይ አንዱ ነው፡፡
የተመድ የልማት ፕሮግራም የ2018 ሪፖርት እንደሚያሳየው ድህነት እያየለባቸው ከመጡ ክልሎች ውስጥ አፋር እና ትግራይ ቀደሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ሌላው አግራሞትን የሚጭረው ደግሞ እአአ በ2010 ከነበረው ደረጃ በ2015 የአፋር ክልል መሻሻሎችን ሲያሳይ በተቃራኒው፤ የልማታዊ መንግስት አቀንቃኞች የወጡባት የትግራይ ክልል ወደ ኋላ መጓዙን ነው፡፡
ምክንያቱም ህወሓት ከራሱ ባለፈ ለማንም ደንታ የሌለው ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ ህወሓት ሲያቀነቅነው የነበረው ‘የልማታዊው መንግስት’ እሳቤ እራሱ ለሚመራው የክልሉ ህዝብ ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ልማት ምን እንደ ሆነ በተግባር ማሳየት ሳይችል ቀርቷል፡፡
ደቡብ ክልል፤ ወይም በአማራ ወይም በኦሮሚያ እንደሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ወይም ከዚያ በባሰ ሁኔታ ተራው የትግራይ ህዝብ በድህነት ሲለበለብ የኖረ- ተመልካች ያጣ ህዝብ ነው፡፡ ለአንድ ሰው በቀን ማግኘት ከሚገባው የምግብ ካሎሪ ጀምሮ በስራ አጥነት፤ በጨቅላ ህጻናት ሞት፤ በትምህርት እና በመሳሰሉት እጅጉን ወደ ኋላ ከቀሩ ክልሎች መካከል የትግራይ ክልል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
Relief Web አለም አቀፉን የምግብ ፕሮግራም ዋቢ በማድረግ እንዳሰፈረው በአንጻራዊነት የሀረሪ ክልል፤ ድሬዳዋ እና ጋምቤላ በቅደም ተከተል የተሻለ የአመጋገብ ስርዓት ያላቸው የተባሉ ሲሆን ትግራይ እና አማራ ያልተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት ያላቸው መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ከሁሉም ደግሞ በትግራይ ክልል ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ እንደሆነ ይጠቅሳል፤ ከ2011 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ብቻ ከነበረበት በ4 በመቶ ማሽቆልቆሉንም ያስረዳል፡፡
ከክልሉ ህዝብ ወደ 25 በመቶ የሚጠጋው ደግሞ በምግብ ራሱን ያልቻለ እና ድጋፍ የሚያስፈልገው ህዝብ ይገኛል፡፡ ይህም ከአማራ እና አፋር ቀጥሎ ሶስተኛ ያደርገዋል፡፡የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (ጥረት) በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኃብት በሚመዘብርበት እና በሚያንቀሳቅስባት ሀገር፤ ህወሓት ሲያስተዳድር በነበረው ክልል ውስጥ ስራ አጥነት መባባሱ ሌላኛው ለጆሮ የሚቀፍ እውነታ ነው፡፡
International Labor Organization (ILO) የኢትዮጵያ ስታቲስትክስ ኤጀሲን ዋቢ አድርጎ እአአ በ2015 ባወጣው ሰነድ የትግራይ ክልል ከአዲስ አባባ ቀጥሎ ስራ-አጥነት የተባባሰበት ክልል ነው፡፡ በክልሉ ያለው የስራ አጥነት ምጣኔ ከሀገራዊው አማካይ የስራ አጥነት ምጣኔ የሚልቅ ነው፡፡ በዚህ እና በክልሉ እየጨመረ በመጣው ድህነት ምክንያት ይላል ሪፖርቱ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ ሀገራት ለስራ ፍለጋ የሚንከራተቱ ዜጎች ከዚህ ክልል በዛ ያለ ቁጥር እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡
ከትግራይም ሆነ ከሌሎች ክልሎች አብዛኛው ስራ ፍለጋ የሚሰደደው ወጣት ደግሞ በ’ልማታዊው’ ህወሓት ዘመነ መንግስት የተወለዱ ናቸው፡፡ በተቃራኒው በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት የህወሓት ባለስልጣናት ልጆች ምናልባትም ድህነት ምን እንደሆነ ወይም ቃሉንም ሰምተው የማያውቁ እና ቅንጡ አኗኗርን የሚመሩ ናቸው፡፡
በአንድ ሀገር የሁለት ዓለም ሰዎች ማለት ይሄው ነው፡፡ እናም ህወሓት አንዱን ክልል ወይም አካባቢን ብቻ ሳይሆን በጋራ ዘርፎናል፤ መዝብሮናል፡፡ ጉዳቱም፤ ህመሙም የጋራ ነው፤ መፍትሄውም እንደዚያው፡፡ ሰላም!