You are currently viewing ያልመከኑ ፈንጅዎች

ያልመከኑ ፈንጅዎች

  • Post comments:0 Comments

በኤደን መብራቱ

ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው፡፡ በዘመን ጅረት ውስጥ አንደኛው ትውልድ የሚጠበቅበትን አበርክቶ ዱላውን ለቀጣዩ ያቀብላል፡፡ በየትግል ምዕራፉም ኃላፊነት የሚረከበው ትውልድ ከተሻለው ልምድ እየወሰደ፤ የጎደለውን ደግሞ እየሞላ በቅብብሎሽ አገር ወደ ከፍታ- ወደ ልዕልና ታቀናለች፡፡ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታም ሆነ የአለም እውነት የሚያስየው ለሀገር-ስለሀገር የለፉ የአገራቸውን ብልጽግና በማረጋገጥ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡

በተቃራኒው በየትውልዱ የሚነሱ አብሪተኞች እና ራስ ወዳዶች የአገራቸውን ጉዞ የኋሊት ሲጎትቱ፤ አገራቸውንም የመበታተን አደጋ ውስጥ በመክተት ለትውልድ የሚተርፍ እዳ ሲያሸክሙ ተመልክተናል፡፡ በእርግጥ ለትውልድ የሚተርፍ፤ አገርንም የሚያሻግር ስራ ለመስራት ከራስ ጥቅም እልፍ ማለትን – ለህዝብ በእምነት መቆምን የሚጠይቅ ስብዕና ባለቤት መሆን ግድ ይላል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ የራሳቸውን ድርሻ አበርክተው ያለፉ የውድ ልጆቿ አሻራ ውጤት ናት፡፡ በተለይም ሀገርን ሊያዋርድ ካሰፈሰፈ ጠላት ያለ ልዩነት በአንድ በመቆም ስለ-ኢትዮጵያ ተዋድቀዋል፡፡ ይህም የአይበገሬነት መሰረት ሆኖ እስከዚህኛው ዘመን ተሻግሯል፡፡ ይህ የውጭ ወራሪን በህብረት አከርካሪውን በመምታት መድረሻ እንደማሳጣት እውነታ እንዳለ ሆኖ ራስን አሸንፎ የውስጥ ሰላምን ጠብቆ በህብረት ሆኖ አገርን መለወጥ፤ ብልጽግናንም ማረጋገጥ ተስኖን ቆይቷል፡፡

ከሁሉም በላይ ቁጭት የሚፈጥረው ደግሞ ጥንታዊትና የብዙ አፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የሆነች አገር ይዘን በሀገር ግንባታ ላይ የተሳካ ስራ መስራት አለመቻላችን ነው፡፡ የመንግስት ስርዓት በተለዋወጠ ቁጥር በአሸዋ ላይ እንደተሰራ ቤት ሁሉም ባዶና አዲስ ጅማሮን የሚፈልግ መሆኑ በታሪካችን ውስጥ መራር እውነታ ነው፡፡

የንጉስ ስርዓት ተገርስሶ-በደርግ ሲተካ፤ የደርግም ተሸኝቶ ህወሓት መራሹ-ኢህአዴግ ቦታውን ሲረከብ ቀውስ በርክቶ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ልጆቿን ገብራለች፡፡ በድህረ-ካሃዲው ህወሓት ኢትዮጵያ ግን ይህንን አዙሪት የምንሰናበትበት ምዕራፍ ተጀምሯል፡፡ በዚህም የሰለጠነ ፖለቲካን የማራመድ፤ ሀገርን በጋራ የመገንባት ፍላጎትም እያየለ መጥቷል፡፡

ይህንን ለማሳካት ግን መንገዶች አልጋ በአልጋ እንዳልሆኑ መገንዘብን ያሻል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል እንደተስተዋለው ካሃዲው ቡድን የሀገርን ካዝና ከመዝረፍ በተጨማሪ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ ፈንጅዎችን ቀብሮ ሄዷል፡፡ ቡድኑ በትውልድ ላይ የቀበራቸው ፈንጅዎች እንዳሰበው ማስተዛዘኛ ሆነው ቡድኑን ባይታደጉትም አደጋውን አሁንም አሳንሶ መመልከት አያስፈልግም፡፡

ቡድኑ ወደ ትግራይ ካጋዘው ፈንጅ የማይተናነስ ድምጽ አልባ ፈንጅዎችን በጥንቃቄ ማየትና ማምከን ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ቡድን ህልውና የተመሰረተባቸው የውሸት ትርክቶች እና በስነ-ምግባር ረገድም የመጣንበት መንገድ እንደ ሀገር ነጥብ ስለማስጣሉ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ፈንጅዎች ካልመከኑ ጊዜ ጠብቀው የሚፈነዱ የሀገረ-መንግስት እና የሀገር ግንባታ ጸር-ናቸው፡፡

በተለይም ህወሓት የፈጠራቸው የውሸት ትርክቶች የሚያመጡትን አደጋ በመገንዘብ፤ ትውልዱ ከዚህ ሴራ ሊያመልጥ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ በነዚህ ትርክቶች ስንራኮት- ለሀገር የረባ ነገር ሳንፈጽም ካሃዲው ቡድን ባዘጋጀልን አዙሪት መመላለሱ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የህወሓት አጥፊ ቡድን በስነ-ምግባር እጅጉን የሚጸየፈውን ሌብነትን የሚያንቆለጳጵስ፤ ከህሊና ጋር መቃረንን ከቁብ እንዳይቆጠር የተጋው ህወሓት ባይሳካለትም በራሱ አምሳል ወንበዴ ትውልድን ለመፍጠር ተግቷል፡፡

የራስን ፍላጎት ለማርካት የሚሯሯጥ ትውልድ፤ አገር ማለት ውሉ ያልገባው ችግርና ሁከት በመፍጠር ውስጥ የራሱን ጥቅም ለማሳደድ የሚራወጥ በህዝብ ስም፤ ህዝብ የሚበድል ጀሌ በየቦታው፤ በየመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተሰግስጎ የመኖሩ ሀቅ የሚታበይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ፤ ለሁላችንም የተመቸች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዙሪያችንን ከማጽዳት፤ ውስጣችንን ከማየት ይጀመራል፡፡

ጀሌዎች እነሱን የሚሸከም አውድ እየተደረመሰ መሆኑን ሲረዱ፤ ጥቅማቸው እንዳይነካባቸው መሯሯጣቸው አይቀርም፡፡ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች፣ የተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ባሉበት አካባቢና መሰል መንግስትና ህዝብ በሚያገናኙ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር እንከን እንዲፈጠር በመስራት ሆን ብሎ ተገልጋዩን ከመንግስት ጋር ከማጋጨት ባለፈ በመንግስት እና ህዝብ ላይ ኪሳራ እንዲደርስ ሙከራ ለማድረግ የሚጥር አካል ይጠፋል የሚል እሳቤ የለኝም፡፡

በመሆኑም ይህንን በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ ተቀብሮ ለውጡን ለመገዳደር የተዘጋጀውን ፈንጅ ቀድሞ በየቦታው ማምከን ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ በአስተዋይነት እና ከእነዚህ አካላት ጋር ባለመተባበር እቅዳቸውን ማምከን አለበት፡፡

በአጠቃላይ በመንግስትም ሆነ በህዝብ ችላ ሊባሉ የማይገቡ እና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የቤት ስራዎች በርካታ ናቸው፡፡ ሀገርንና ትውልድን እስከወዲያኛው እንደ ሸረሪት ድር ተብትቦ ለመያዝ ህወሓት የዘረጋቸው ወጥመዶችአሁንም ሊበጣጠሱ ይገባል ለዚህ ደግሞ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡

ምላሽ ይስጡ