/ከፍኖተ አዲስ/
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የህግ ማስከበር ኦፕሬሽን ፣በጀግናው መከላከያችን ላይ ስላደረሰው የክህደት ጥቃት እንዲሁም በማይከደራ ወንጀለኛው ቡድን ሳላደረሰው ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ለደቡብ አፍሪካ መንግስት ማስረዳቱን ተከትሎ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያውና አንዳንድ ሚዲያዎች በተለይ DW መንግስት ለመስማማት ፈቃደኛ ሆኗል ብሎ የበሬ ወለደ ዜና ሲያራግቡ ውለዋል፡፡
መንግስት ድርድር ሳይሆን ህግን ብቻ እንደሚያስከብር በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡የመንግስታችን ቁርጥ ያለ ሀሳብ ይሄው ነው፡፡ ሰለሆነም መረጃው መሰረት የሌለው ወሬ ብቻ ነው፡፡
ወንጀለኛው ቡድን ከታሪኩ መረዳት እንደሚቻለው አንድም ቀን በጠረንጴዛ ዙሪያ ተደራድሮ ለችግሮች መፍትሄ አምጥቶ አያውቅም፡፡ ድርድሩን የሚፈለግው ጊዜ ለመግዛት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሀገራችን ሰላም ናፍቋታል፡፡ ነገር ግን ከወንጀለኛ ቡድን ጋር በመደራደር ሰላም አይመጣም፡፡ ዘላቂ ሰላም የሚመጣው ወንጀለኞችን በመቀጣት ብቻ ነው፡፡የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ የሚሰማ መንግስት ነው ህዝቡ ተደራደርልኝ ሳይሆን ህግ አስከብርልኝ እያለ ነው ይሄን ነው መንግስት እያደረገ ያለው እንጅ ድርድር የሚባል ነገር የለም፡፡
መንግስት ይሄን ጁንታ ወንጀለኛ ቡድን ለ27 ዓመታት የሰራውን ግፍ ትቶ ለባለፉት ሁለት አመታት እንደመርና ሀገራችንን ወደ ዲሞክራሲና የብልጽግና ጎዳና እንውሰዳት ብሎ ሲጠይቀው ቆይቷል፡፡ ጁንታው ግን ከመነሻው የክፋት መንገድን የሚከተል ነበርና የመንግስትን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ሀገርና ህዝብን ሲያሸብር ቆይቶ በመጨረሻም ቀዩን መስመር ወደ ማለፍ ተሸጋገረ፡፡ ትላንት በሀገራችን ወግና ባህል መሰረት የሀገር ሽማግሌዎች ሲለመኑት የሀገር ሽማግሌዎችን ለደርድር ዘገያቹህ በማለት ለመሳለቅ የሞከር ቡድን ታዲያ አሁን በምን ሞራሉ ነው ለመደራደር የሚሯሯጠው? የጨነቀለት አደራደሩኝ ማለት አይሰራም፡፡
እንደራደር ብንል እነዛ እጅና እግራቸው ወደ ኋላ ታስሮ በግፍ የተረሸኑት የሰሜን እዝ ጀግኖችን መካድ ይሆናል፤ እንደራደር ብንል የእለት ጉርሳቸውን ለማገኘት ደፋ ቀና ሲሉ በነበሩ የማይካድራ ወጣቶችና በንጹሀን የማይከደራ ነዋሪዎች ደም መቀልድ ይሆናል ፡፡ እንደራደር ማለት ጁንታው በሀገራችን በየቦታው የሽብር ጥቃቶችን ከጀርባ ሆኖ በገንዘብ እየደጎመ ንጹሀን ዜጎች ሲጨፈጨፉ እንዲኖሩ መፍቀድ ነው ፡፡ስለዚህ እንደራደር የምንልበት ሞራል የለንም፡፡ በአገር ለመጣ በአገር አንደራደርም፡፡
ሲጀመር ድርድር ሀገር ከሀገር ፣መንግስት ከመንግስት እንጅ ከአንድ ወንበዴ ቡድን ጋር ሊሆን አይችልም እላለው፡፡ ያለን ጠንካራ ሀገርን የሚመራ ጠንካራ መንግስት ነው ስለሆነም በአንድ የአገራችን ክፍል ውስጥ የተፈጠረ ወንጀልን በህጉ መሰረት መዳኘት እንጅ ከስሩ እስከወዲያኛው ለመገርሰስ አንደ ሀሙስ ከቀረው ወንጀለኛው ጁንታ ቡድን ጋር መንግስት ለድርደር የሚቀመጥበት አግባብ አይኖርም፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይ ከተሞች ነጻ እየወጡ ይገኛሉ በዛሬ ውሎ እንኳ አዲግራት ሙሉ በሙሉ በጀግናው መከላከያችን ቁጥጥር ስር መሆኗን የምስራች ሰምተናል፡፡ በአጠቃላይ ወንጀለኛው ቡድን ዙሪያውን ተከቦ የመጨረሻው ሰዓት ደርሶበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነገሮች እየቀለሉና መንግስት ህግ ማስከበሩን እያጠቃለለ ባለበት ሰዓት መንግስት እደራደራለው ብሏል የሚለው ወሬ መሰረተ ቢስ ነው፡፡
ድል ለሰራዊታችን !