ከሀዲው የህወሓት ቡድን ፍቅርም ይቅርታም ስለማያውቅና ህግ ማስከበር የመንግስት ግዴታ ስለሆነ በሚገባው ቋንቋ በቡድኑ ላይ እርምጃ መውሰዱን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመለስ አብዲሳን ጨምሮ የክልል አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት በክለሉ ፕሬዝዳንት ፅ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ “ለመከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ” በሚል ከኪነጥበብ ባለሙያዎች የተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው አክብረዋል። በዕለቱ የተከናወነው መርሃ ግብር በክልሉ የፖሊስ ማርሽ ባንድ የታጀበ ሲሆን፤ የደም ልገሳን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከብሯል፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመረሃ ግብሩ ላይ ባገረጉበት ንግግር እንደገለፁት ከሀዲው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱ ውስጥ የሴራእንቆቅልሾችን ፈጥሮ ህዝቡን በመለያየት ሀገር ሲያፈርስ ቆይቷል። በአገራዊ የለውጥ ጉዞ በይቅርታ ሁሉን ትተን ወደ ፊት እንራመድ በሚል ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ከሀዲው ቡድን ሊቀበለው አልቻለም።ይህ ከሀዲ ቡድን ከመፈጠሩ አንስቶ በተንኮልና በጥላቻ የተሞላ ስለሆነ ባሳለፍናቸው ሁለት አመታት ብዙ ተንኮሎችን ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁን ግን ለመናገር እንኳን በሚከብድ መልኩ በመከላከያ ሰራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት መፈፀሙ በታሪክ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም ብለዋል፡፡ ከሀዲው ቡድን የእጁን ማግኘት አለባበት ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ለዚህ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝቡ ከፌድራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ህግ የማስከበር ስራውን በመደገፍ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ለዚህ የከሀዲ ቡድን ተላላኪ የሆኑ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉትን ጠርገን እያፀዳን ነው ያለነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ በኋላ በሀገሪቷ የሰላምና የዴሞክራሲ ንፋስ እንዲነፍስ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የፌድራል መንግስት በቅንጅት ሌትና ቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
