You are currently viewing በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የፓርቲዎች ሚና ወሳኝነት

በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የፓርቲዎች ሚና ወሳኝነት

  • Post comments:0 Comments

ቢያ ሉቡኮ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሰረቱባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የሚወክሉት የህብረተሰብ ፍላጎት በመንግስት ፖሊሲዎች እንዲካተትላቸው የተደራጀ ግፊት ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የሚወክሉትን ህዝብ ፍላጎት በፓርላማ ወንበር ይዘው ለማንፀባረቅና መንግስታዊ ውሳኔ እንደያገኙ ማስቻል፤ መታገል ነው፡፡ በዋነኛነት ግን ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት ራሳቸውን ችለው ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በማበር መንግስት መስርተው በአስፈፃሚው፤ በህግ-አውጪውና በዳኝነት የህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው ሚናቸውን እንዲጫወቱ በመፈለግ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች አፈጣጠር ፅንሰ-ሃሳብና ተግባር የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ሌላው የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ደግሞ ለዴሞክራሲ ዕድገትና ልማት የሚጫወቱት ሚና የሚጠቀስ ነው፡፡ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል፡፡ ፓርቲዎች ለግለሰቦች የንቃተ-ህሊና ዕድገት፤ በግለሰቦች መካከል ሊኖር ስለሚችለው ግንኙነትና የጋራ ግንባታ በአጠቃላይ ሃሳብ ልዕልና ግንባታ ዙሪያ የሚያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ስለ ዴሞክራሲ ከመስበኩ በፊት ውስጡን በዴሞክራሲና በዴሞክራሲያዊ መርሆችና ተግባራት ማነፅ ይጠበቅበታል፡፡ በውስጡ ነፃና በእኩልነት መርህ ያልታነፀ ፓርቲ ህይወት አልባ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ፓርቲ ለማህበረሰቡ የሚተርፍ ነገር የለውም፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ አሸናፊነት፤ በክርክር ማመን፤ በአብዘኛው ድምፅ መገዛትን ለአባሎቻቸው በማስተማር ለቀረው ህዝብ ትሩፋት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቁጥር ከፍተኛ ነገር ግን በጥራት ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ሁሉም ፓርቲ ስልጣን መያዝ ይፈልጋል፡፡ ሁሉም የህዝብ ድምፅ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ አብዛኛው በጥላቻ ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ተወልዶ ያደገ ነውና ይህንኑን ያንፀባርቃል፡፡ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ለውጥ የተባበረ ሀይል ከገዥም ከተፎካካሪ ፓርቲም ይፈለጋል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ የሚታየው ዓይነት የተበታተነ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፓርቲ አያስፈልጋትም፡፡ ሁሉም ፓርላማ ቢገቡም የተረጋጋ መንግስትና ህዝብ ለመፍጠርና ለመምራት የሚያስችላቸው አይሆንም፡፡ ከመቶ በላይ ርዕዮተ ዓለምም በዓለም ደረጃ የለም፡፡ ሃይላቸውን አሰባስበው፤ መተባበርን ባህል አድርገው፤ ለአገር የሚበጅ ወደፊት ተመልካች የሆነ አስተሳሰብ ሰንቀው ለ2013 ዓ.ም ምርጫ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ 6ኛው የፓርላማ ዘመን የተለያዩ ዋና ዋና ድምፆች የሚደመጡበት ይሆን ዘንድ የእያንዳንዱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ህዝቡም ይህን ይጠብቃል፡፡

ምላሽ ይስጡ